ቀጥታ፡

የንብ ሃብት ልማት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ከማሳደግ ባለፈ የሥራ እድል እየፈጠረ ነው

ዲላ፤ ግንቦት 11/2018 (ኢዜአ)፦የንብ ሃብት ልማት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ከማሳደግ ባለፈ የሥራ እድልን በመፍጠር ረገድ ያለው ድርሻ መጨመሩ ተመላከተ።

ዓለም አቀፍ የንብ ቀን በክልል ደረጃ በዲላ ከተማ በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ነው።


 

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትንና ዓሣ ሀብት ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ አዚዝ አያሌው በወቅቱ እንዳሉት፤ ንብ ከማር ምርት ባሻገር የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግና የተፈጥሮ ሚዛንን ለመጠበቅ ሚናዋ የጎላ ነው።

የንብን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ለማስፋት በተደረገ ጥረት ልማቱ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ከማሳደግ ባለፈ የሥራ እድልን በመፍጠር ረገድ ያለው ድርሻ መጨመሩን አመልክተዋል።

አምራችና አቅራቢዎችን ጨምሮ ባለድርሻ አካላትን በማቀራረብና በማቀናጀት የዘርፉን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በክልሉ የንብ ሃብት ልማት አማራጭ የሥራ እድል ፈጠራ ምንጭ በመሆን የአምራቹን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ መቻሉን ያነሱት ደግሞ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የዲላ ክላስተር ማስተባበሪያ አማካሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበባየሁ ኢሳያስ ናቸው።

በተለይ የተራቆቱ ተራራዎችን በተፋሰስ በማልማት ለንብ ሃብት ልማት መዋሉንና በዚህም 125 ኢንተርፕራይዞች እና በዘርፉ ሦስት ዩኒየኖችን  ወደ ሥራ ማስገባት መቻሉን ገልጸዋል።

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ከ200 በላይ እጽዋቶችን ያቀፈው የጌዴኦ መልክዓ ምድር ለንብ ሃብት ልማት ምቹ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በዞኑ በንብ ሃብት ልማት ያለውን ጸጋ ለመጠቀም በተለይ ዝቅተኛ የእርሻ መሬት ላላቸው አርሶ አደሮች የግብዓትና የሙያ ድጋፍ በመስጠት ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን አንስተዋል።

በዚህም በዓመት ከ4 ሺህ ቶን በላይ የተጣራ ማር ለገበያ ከማቅረብ ባለፈ በቡና ተፈጥሯዊ ማር አለም አቀፍ እውቅና በማግኘት ለውጭ ገበያ እየቀረበ ነው ብለዋል።

ዓለም አቀፉ የንብ ቀን በፓናል ውይይት፣ በማር ኤግዚቢሽንና በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም