በክልሉ የቱሪዝም ሀብቶችን ለይቶ ጥቅም ላይ ለማዋል የተሰሩ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት አምጥተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የቱሪዝም ሀብቶችን ለይቶ ጥቅም ላይ ለማዋል የተሰሩ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት አምጥተዋል
ወላይታ ሶዶ፤ ግንቦት 11/2018 (ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ያሉ የቱሪዝም ሀብቶችን በመለየት፣ በማልማትና ለጎብኚዎች ምቹ በማድረግ ረገድ በተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።
ባለፉት ዓመታት የለውጡ መንግስት እንደ ሀገር ተግባራዊ ያደረገው የብዝሃ-ዘርፍ ኢኮኖሚ ግንባታ ፖሊሲ በኢትዮጵያ ለዓመታት ሳይታወሱና ሳይለሙ የቆዩ እምቅ የተፈጥሮና የሰው ሰራሽ ጸጋዎችን አውጥቶ ጥቅም ላይ ለማዋል አስችሏል።
የተፈጥሮ ጸጋዎችን ለማልማት በተከናወኑ የተቀናጁ ተግባራትም ተጨባጭና ስኬታማ ውጤት እየተመዘገበ ነው።
ኢኮኖሚውን ከአንድ ዘርፍ ጥገኝነት ለማውጣት በተነደፈው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕቅድ ውስጥ ቱሪዝም አንዱና ዋናው የኢኮኖሚ ምሶሶ ተደርጎ ትኩረት ተሰጥቶታል።
በሀገሪቱ ዕምቅ የቱሪዝም ሀብቶች ከሚገኙባቸው አካባቢዎች መካከል ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አንዱ ሲሆን ክልሉ ሀብቶቹን ወደ ውጤት በመቀየር ረገድ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን በማስመልከት ኢዜአ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ጋር ቆይታ አድርጓል።
ርዕስ መስተዳድሩ አቶ ጥላሁን ከበደ እንዳሉት፤ በክልሉ የሚገኙ ዕምቅ የቱሪዝም ሀብቶች ተለይተው እንዲተዋወቁና የልማቱ አካል እንዲሆኑ ሀገራዊ ለውጡ ምቹ መደላድል ፈጥሯል።
ቀደም ሲል ለቱሪዝም ዘርፍ ብዙም ትኩረት ባለመሰጠቱ ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅኦው የጎላ እንዳልነበር አስታውሰው፣ ለውጡን ተከትሎ በተሰጠ ትኩረት በክልሉ ያሉ የቱሪስት ሀብቶችን ለይቶ የማልማትና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የማሳደግ ሥራ መሰራቱን ተናግረዋል።
እንደ ሀገር ለቱሪዝም ዘርፍ እየተሰጠ ያለው ትኩረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣት በክልሉ የቱሪዝም ልማት ላይም የራሱን አበርክቶ ማድረጉን አቶ ጥላሁን ገልጸዋል።
በክልሉ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች ባህላዊ እሴቶች እንዲሁም ሀይማኖታዊና ታሪካዊ ስፍራዎች እንዳሉ ገልጸው፣ እነዚህ የቱሪዝም ሀብቶች ለኢኮኖሚው እድገት አስተዋፅኦ እንዲኖራቸው በልዩ ትኩረት ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል።
በዚህም በክልሉ ከዘርፉ የሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እያደገ መምጣቱን ጠቁመው፣ በቀጣይም ይህን ውጤት በማስቀጠል የዘርፉን ፋይዳ ለማሳደግ ይሰራል ብለዋል።
እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ፣ በክልሉ የመስህብ ስፍራዎችን የማልማትና የማስተዋወቅ እንዲሁም የመጠበቅ ሥራዎች በቅንጅት እየተከናወኑ ሲሆን ይህም የጎብኚዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አድርጓል።
ባለሀብቶችም ትልልቅ ሆቴሎችን ጨምሮ ደረጃቸውን የጠበቁ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በመገንባት በቱሪዝም ዘርፉ ክልሉም ሆነ ሀገር ተጠቃሚ እንዲሆኑ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ ያለፉት ዘጠኝ ወራት በክልሉ ያሉ የቱሪስት መስህቦችን ከጎበኙ ከ43 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥና የውጪ ሀገር ጎብኚዎች 480 ሚሊዮን ብር ገቢ መገኘቱንም ለማወቅ ተችሏል።