ቀጥታ፡

ትውልዱ የአካባቢውን ልምላሜ ጠብቆ በማቆየት የማህበረሰቡን የደን ልማት ባህል ማስቀጠል አለበት-የሀገር ሽማግሌዎች 

ጂንካ፤ ግንቦት 11/2018 (ኢዜአ)፦ትውልዱ የአካባቢውን ልምላሜ ጠብቆ በማቆየት የማህበረሰቡን የደን ልማት ባህል ለማስቀጠል ግንዛቤን እየፈጠሩ መሆኑን የአሪ የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአሪ ማህበረሰብ ደኖችን ጠብቆ የማቆየትና የመንከባከብ ጠንካራ ባህል አለው።

በዞኑ ሰሜን አሪ ወረዳ የጎዛ ቀበሌ የሀገር ሽማግሌዎችም ትውልዱ የአካባቢውን ልምላሜ ጠብቆ በማቆየት ለመጪው ትውልድ እንዲያሻግር ግንዛቤ በመፍጠር ደኖችን የመንከባከብ ባህሉን ለማስቀጠል እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የሃገር ሽማግሌ አቶ ተክሌ ተረፈ እንደገለፁት፤ በአካባቢው ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሻገር የቆየ ደኖችን የመንከባከብ እና ጠብቆ የማቆየት ባህል አለ፡፡


 

ባህሉ ሳይሸራረፍ እንዲቀጥል በደን ተከላና እንክብካቤ ከማሳተፍ ባለፈ የደኖች መኖር ያለውን ጠቀሜታ በተመለከተ ግንዛቤ የመስጠትና የማስተማር ስራ እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በእርሻ ስራ ውጤታማ ለመሆን ደኖችን ጠብቆ ማቆየት ተገቢ መሆኑን ጠቁመው ደን ከሰው ልጅ ህይወት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ስላለው እንክብካቤ እንደሚያስፈልገውም አስረድተዋል።

ደኖች የተራቆቱባቸው አካባቢዎች በተፈጥሮ አደጋዎች በተደጋጋሚ ሲፈተኑ አስተውለናል ያሉት ደግሞ የሀገር ሽማግሌው ብላታ ቶዳ ናቸው።

አዲሱ ትውልድ ይህን በመገንዘብ ደኖችን እንዲንከባከብ፣ በተራቆቱ አካባቢዎች ችግኞችን እንዲተክሉ ግንዛቤ በመፍጠር ትውልዱን የማነፅ ስራ እየሰሩ እንደሚገኙም ገልጸዋል።


 

የአሪ ባህላዊ የዕርቅ ስነ-ስርዓት፣ አፈ-ታሪኮች፣ የመጪው ዘመን ትንበያ እና ሌሎች ባህላዊ ስነ-ስርዓቶች የሚፈፀሙት በደኖች አካባቢ በሚገኝ ትልቅ ዋርካ ስር እንደሆነ የገለፁት ደግሞ አቶ  አለማየሁ ታጋ ናቸው።

በደኖች አካባቢ የሚፈፀሙ ባህላዊ ስርዓቶች የደኖችን ጥቅም ለአዲሱ ትውልድ ለማስተማር ታስቦ እንደሆነም አመልክተዋል።

ደኖች ከሰው ልጅ ህልውና ጋር የተቆራኙ በመሆናቸው አዲሱ ትውልድ ይህን ተገንዝቦ የአካባቢውን ለምላሜ ጠብቆ እንዲያቆይ የማስተማር ስራ እየሰራን ነው ብለዋል።

በአሪ ዞን የአካባቢ ጥበቃ እና የአየር ንብረት ለውጥ ጽህፈት ቤት የደን ጥበቃና ቁጥጥር የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ክንዴ ፍሰሃ በዞኑ ደኖችን ጠብቆ ለትውልድ የማሻገር ጠንካራ ባህል እንዳለ ገልፀዋል።


 

በዞኑ ከ21 ሺህ 700 ሄክታር በላይ መሬት በደን መሸፈኑን ጠቁመው በዚህም 41 ጥብቅ የተፈጥሮ ደኖች እንደሚገኙ ተናግረዋል። 

በአካባቢው በሚገኘው ደን ውስጥም ለመድኃኒትነት የሚያገለግሉ በርካታ የዕፅዋት ዓይነቶች እንዳሉም አስረድተዋል።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በዞኑ ከ12 ሚሊዮን በላይ ችግኞች በተራቆቱ አካባቢዎች የሚተከሉ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅትም የአካባቢው የደን ሽፋን እያደገ መምጣቱን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም