ዩኒቨርሲቲው የ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030"ን ሀገራዊ ራዕይ ለማሳካት በትኩረት እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው የ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030"ን ሀገራዊ ራዕይ ለማሳካት በትኩረት እየሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 11/2018 (ኢዜአ)፦ዩኒቨርሲቲው የመንግሥት ተቋማትን የዲጂታላይዜሽን አቅም በማሳደግ የ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030"ን ሀገራዊ ራዕይ ለማሳካት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ንጉሥ ታደሰ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን በተያዘው በጀት ዓመት ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገትን ከመተንበይ ባለፈ የፋይናንስ አካታችነትን ያረጋግጣል፣ ለወጣቶች ሰፊ የስራ እድል ይፈጥራል፣ እንዲሁም የመንግስት አሰራርን በማሳለጥ የዜጎችን ህይወት ያቃልላል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን ከግብ ለማድረስም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና ከፍተኛ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ንጉሥ ታደሰ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተወዳዳሪነት ይበልጥ ለማሳደግ በዲጂታላይዜሽን ራሷን ለማብቃት እየተጋች ነው፡፡
ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
የመንግሥት ተቋማትን አሰራር ማዘመን እና የአገልግሎት አሰጣጥን ማቀላጠፍ ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከተሰጡት ሀገራዊ ተልዕኮዎች መካከል ቀዳሚው በመሆኑ ይህንን ለማሳካት የዲጂታላይዜሽን አማራጭ ፍቱን መፍትሄ ነው ብለዋል፡፡
የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ልማት ለማፋጠን እየተተገበረ ያለውን የዲጂታል ስትራቴጂ ስኬታማ ለማድረግ፣ ተቋሙ የመንግሥት ተቋማትና ቴክኖሎጂ የሚተሳሰሩበትን አቅም ለመገንባት በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ከእነዚህም መካከል የዩኒቨርሲቲውን የውስጥ አሰራርና የስልጠና አሰጣጥ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ማድረግና የመንግሥት ተቋማት የዲጂታል አሰራርን የተላበሰ አገልግሎት መስጠት የሚችሉበትን አቅም ለመፍጠር የሚያስችል ልዩ ኮሌጅ በማደራጀት ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
እንዲሁም በዘርፉ ብቁና ተወዳዳሪ የሆኑ መምህራንን የማፍራት ሥራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የመንግሥት ተቋማት ሥራቸውን ውጤታማ በሆነ መንገድ ማከናወን እንዲችሉ ከዲጂታል ዘርፍ ጋር የተቆራኙ አዳዲስ የስልጠና ፕሮግራሞችን ለመክፈት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለአብነትም የአይቲ ኢንፍራስትራክቸር እና ሳይበር ሴኪውሪቲ ትምህርት ክፍልን ለመክፈት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የዲጂታል አገልግሎትን ማስፈንና በዘርፉ ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት ከተቻለ፣ የመንግሥትን አሰራር ከማዘመንም ባለፈ ብልሹ አሰራርንና ሙስናን በዘላቂነት ለመቅረፍ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር አስገንዝበዋል።