የኢትዮጵያ ልዑክ የባኩ ጉብኝት ለከተማ ልማት፣ ዕድሳትና ቅርስ ጥበቃ ስራዎች ትልቅ ልምድ የተወሰደበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ልዑክ የባኩ ጉብኝት ለከተማ ልማት፣ ዕድሳትና ቅርስ ጥበቃ ስራዎች ትልቅ ልምድ የተወሰደበት ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 11/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን የአዘርባጃን ባኩ ጉብኝት ለከተማ ልማት፣ ዕድሳትና ቅርስ ጥበቃ ስራዎች ተጨማሪ ትልቅ ልምድ የተወሰደበት መሆኑን የአዲስ አባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባዋ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ባኩ እጅግ ጽድት ያለችና ማራኪ ከተማ መሆኗን ገልጸው፤ ጥንታዊቷ ከተማ (The Old City) በመባል የሚታወቀው የከተማዋ ክፍል በጥንቃቄ ታድሶ ለጉብኝት ክፍት መደረጉን ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ከዚህ ቀደም ጥቁሯ ከተማ (The Black City) ይባል የነበረውን አሮጌና ጎስቋላ ስፍራ፣ ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ ሙሉ በሙሉ በማፍረስና እንደ አዲስ በመገንባት፣ አዲሲቷንና ውቢቷን ከተማ ነጭ ከተማ (White City-Baku) በሚል ስያሜ እውን ማድረግ መቻላቸውን አመልክተዋል።
ይህ የባኩ ከተማ እድሳት ሂደት የኢትዮጵያንም ተሞክሮ የሚያንፀባርቅ መሆኑን የገለጹት ከንቲባዋ፣ እኛም ታሪክንና ቅርሶቻችንን ጠብቀን እያደስን፣ ጎስቋላ አካባቢዎችን ደግሞ አፍርሰን በአዲስ መልክ በመገንባት ላይ እንገኛለን ብለዋል።
ለአብነት ያህልም፣ ቅርሶችን በማደስና ለቀጣዩ ትውልድ በማሻገር ረገድ፤ በፒያሳ እና በአራት ኪሎ አካባቢ ያሉ ጥንታዊ ሕንፃዎችን፣ የመጀመሪያውን ሲኒማ ቤት፣ የመጀመሪያውን ማዘጋጃ ቤት፣ ብሔራዊ ቤተ መንግሥትን እንዲሁም የተለያዩ ሐውልቶችን ማደስ መቻሉን ጠቁመዋል።
ከዚህም ባሻገር እንደ ሐረር ጀጎል ግንብ፣ የጅማ አባጅፋር ቤተ መንግሥት፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እና የጎንደር ፋሲል ቤተ መንግሥት የመሳሰሉትን ታላላቅ ቅርሶች በማደስ ላይ እንገኛለን ሲሉ ገልጸዋል።
በተጓዳኝም፣ እጅግ ጎስቋላና ለመኖር ምቹ ያልነበሩ መንደሮችን በማፍረስ ዘመናዊና ምቹ በሆነ መልኩ በድጋሚ መገንባቱን ነው ከንቲባዋ ያስታወቁት።
በተለይም በቅርቡ በመዲናችን አዲስ አበባ እና በሌሎች የሀገራችን ከተሞች በተሳካ ሁኔታ የተተገበረው ሰፊ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት የዚሁ የከተማ እድሳትና ማስዋብ ራዕይ ዋነኛ ማሳያ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም ስራ ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ይበልጥ ምቹ፣ ማራኪ፣ አረንጓዴ እና ዘመናዊ ለማድረግ መቻሉን አመልክተዋል።
የመንገድ መሰረተ ልማቶችን ከማስፋት፣ ለእግረኛና ለብስክሌት ምቹ የሆኑ አካባቢዎችን ከመፍጠር እንዲሁም የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር አኳያ እጅግ አበረታችና ተጨባች ውጤት ተመዝግቦበታል ብለዋል።
በአጠቃላይ ይህ የባኩ ጉብኝት፣ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተጀመሩትን የከተማ ልማት፣ እድሳትና የቅርስ ጥበቃ ስራዎች ይበልጥ አጠናክረን እንድንቀጥል ተጨማሪ ትልቅ ልምድ የተቀሰመበት ጠቃሚ ጉብኝት ነበር ሲሉ ከንቲባዋ አስታውቀዋል።