ቀጥታ፡

ጠቅላላ ምርጫው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር ጉልህ ፋይዳ አለው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 11/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር ጉልህ ፋይዳ እንዳለው የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፎረም ገለጸ።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የጠቅላላ ምርጫ ሂደቱን ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊነት ለማረጋገጥ በምርጫ ታዛቢነትና መራጮች ትምህርት በንቃት እየተሳተፉ መሆናቸውን ፎረሙ አስታውቋል።

በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለምርጫ ታዛቢነት ዕውቅና የተሰጣቸው 55 የሀገር ውስጥ ድርጅቶችም በተለያዩ አካባቢዎች ከ60 ሺህ 277 በላይ ወኪሎችን አሰማርተዋል።

በመራጮች ትምህርት ላይ ዕውቅና የተሰጣቸው 169 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችም ለመራጩ ህዝብ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርትና ስልጠና እየሰጡ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፎረም ዋና ዳይሬክተር ጌትነት ካባ እንዳሉት፤ ምርጫ ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ያላቸውን የባለቤትነት ስሜት የሚያረጋግጡበት መሣሪያ ነው።

የኢትዮጵያን ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊነት ለማረጋገጥም ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ  ጋር በመተባበር በታዛቢ፣ በትምህርትና ስልጠና ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በምርጫው ዕለትም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በታዛቢነት በማሰማራት የሂደቱን ዴሞክራሲያዊነት እንዲከታተሉ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

ለዜጎችም በምርጫ ሂደት የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ሕገ-መንግሥታዊ የመምረጥ መመረጥ መብታቸውን በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል ትምህርት እየተሰጠ መሆኑንም  አንስተዋል።

በዚህም ዜጎች ሀገርን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ያሸጋግራል ብለው ለሚያምኑት ፓርቲ ድምፅ ለመስጠት በቂ ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የምርጫውን ዴሞክራሲያዊነት ለማስጠበቅም ዜጎች የፖለቲካ ፓርቲዎችን የመገናኛ ብዙኅንና የአደባባይ ምረጡኝ ቅስቀሳን በሚገባ በመከታተል በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ መስጠት አለባቸው ብለዋል።

የምርጫ ካርድ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ጉዳይ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እንዲያብብ ማድረግ የሚያስችል ጤናማ ፉክክር ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር ጉልህ ጠቀሜታ እንዳለውም ገልጸዋል።

በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንቦት 24/2018 ዓ.ም መራጮች ድምፅ ይሰጡበታል ተብሎ የሚጠበቀው ጠቅላላ ምርጫ አስራ ሶስት ቀናት ቀርተውታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም