ቀጥታ፡

የዓለም ዋንጫ ተስፋን ለማለምለም የሚደረግ ፍልሚያ፤ ቀይ ቀበሮዎች ከካርቴጅ ንስሮች

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 11/2018 (ኢዜአ)፦ በ16ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ የመጨረሻ ጨዋታዋን ዛሬ ከቱኒዚያ ጋር ታከናውናለች።

ጨዋታው ምሽት አራት ሰዓት ላይ በመሐመድ ስድስተኛ እግር ኳስ አካዳሚ ይካሄዳል።

በአሜሪካዊው አሰልጣኝ ቤንጃሚን ዚመር የሚመራው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በምድብ አንድ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲሸነፍ በቀሪው መርሐ ግብር አቻ ተለያይቷል።

ከግብጽ ጋር ያለ ግብ አቻ ሲለያይ በአዘጋጇ ሞሮኮ 2 ለ 1 ተሸንፏል።  ብሔራዊ ቡድን በአንድ ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ቡድኑ ከሞሮኮ ጋር በነበረው ጨዋታ የተሻለ እንቅስቃሴ አድርጓል።

ተጋጣሚዋ ቱኒዚያ ከሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ በማግኘት ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።

ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ዓለም ዋንጫ የማለፍ ህልሟን ለማለምለም የግድ ቱኒዚያን ማሸነፍ ይጠበቅበታል።

ቀይ ቀበሮቹ ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ካጠናቀቁ ቀጥታ በኳታር ለሚካሄደው የፊፋ ከ17 ዓመት በታች ዓለም ዋንጫ በቀጥታ ያልፋሉ።

በአንጻሩ ሶስተኛ ከወጡ ወደ ዓለም ዋንጫ ለማለፍ ወደ ሚደረገው ማጣሪያ ይሸጋገራሉ።

አሰልጣኝ ቤንጃሚን ዚመር ከጨዋታው በፊት በሰጡት አስተያየት አላማቸውን ለዓለም ዋንጫ ማለፍ መሆኑን ተናግረዋል። ለዚህም እየሰራን ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ብሔራዊ ቡድኑ እስከ መጨረሻው እንደሚፋለም እና ቱኒዚያን ለማሸነፍ እንደሚጫወት ተናግረዋል።




ቡድኑ ከጨዋታው በፊት የመጨረሻ ልምምዱን ትናንት በመሐመድ ስድስተኛ አካዳሚ ማከናወኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

በዚሁ ምድብ በተመሳሳይ ከምሽቱ አራት ሰዓት አዘጋጇ ሞሮኮ ከግብጽ ጋር ትጫወታለች።

ሞሮኮ እና ግብጽ በተመሳሳይ አራት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ይዘዋል።

ጨዋታው በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀ ሁለቱ ሀገራት በቀጥታ ወደ ዓለም ዋንጫ ማለፋቸውን ያረጋግጣሉ።

ጨዋታውን የሚያሸንፈው ቡድን ለዓለም ዋንጫ ከማለፍ ባለፈ ምድቡን በመሪነት ያጠናቅቃል።

ሽንፈት የሚያስተናግደው ብሔራዊ ቡድን በሂሳባዊ ስሌት ወደ ዓለም ዋንጫው የመግባት እድል አለው።

16ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ እስከ ግንቦት 25 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።

በአፍሪካ ዋንጫው ከሚሳተፉ 16 ሀገራት መካከል የተሻለ ውጤት የሚያስመዘግቡ 10 ሀገራት በጥቅምት እና ህዳር ወር 2019 ዓ.ም በኳታር ለሚካሄደው 20ኛው የፊፋ ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ያልፋሉ።

በዓለም ዋንጫው 48 ሀገራት ይሳተፋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም