በክልሉ የጤና ተቋማትን አቅም በማጎልበት የበሽታ መከላከልና አክሞ የማዳን ተግባራትን በውጤታማነት ማከናወን ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የጤና ተቋማትን አቅም በማጎልበት የበሽታ መከላከልና አክሞ የማዳን ተግባራትን በውጤታማነት ማከናወን ተችሏል
ሀረር ፤ ግንቦት 11/2018 (ኢዜአ)፦ በሀረሪ ክልል የጤና ተቋማትን አቅም በማጎልበት የበሽታ መከላከልና አክሞ የማዳን ተግባራትን በውጤታማነት ማከናወን መቻሉን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለጸ፣
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብዲ አሚን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ በየደረጃው በሚገኙ የጤና ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶች ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑና የህብረተሰቡን እርካታ በሚያረጋግጥ መልኩ እንዲከናወኑ መደረጉን ተናግረዋል።
መድኃኒቶችና የህክምና ግብዓቶች ሳይቆራረጡ ለታካሚዎች እንዲደርሱ በተደረገው የተቀናጀ ጥረት ስኬት መገኘቱን አስታውቀዋል።
ወረርሽኝ ሳይከሰት አስቀድሞ ለመለየትና ከተከሰተም በኋላ ጉዳት ሳያደርስ ለመቆጣጠር የሚያስችል የቅኝት ስርዓት ውጤታማ ሆኗል ብለዋል።
የጤና ባለሙያዎችን በዕውቀትና በክህሎት ማብቃት በመቻሉም ዘርፉን ወደ ላቀ ምዕራፍ ማሸጋገር ተችሏል ብለዋል።
በጤና ኬላዎች ይሰጡ የነበሩ የጤና ኤክስቴንሽን መርሐ-ግብሮችን ወደ አጠቃላይ የጤና ማዕከል ደረጃ በማሸጋገር ህብረተሰቡ ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አብራርተዋል።
በክልሉ በገጠርና በከተማ የሚገኙ የጤና ተቋማትን ደረጃ ለማሻሻል የሕንጻ ግንባታዎችን በማስፋፋት፣ ዘመናዊ የሕክምና ግብዓቶችንና ቁሳቁሶችን በማሟላት፣ እንዲሁም የሰለጠነ የሰው ኃይል በበቂ ሁኔታ በማሰማራት ለሕብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት የመስጠት ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ህብረተሰቡ ክትባት እና የወሊድ ክትትልን ጨምሮ ሌሎች መሠረታዊ የሕክምና አገልግሎቶችን በቅርበት ማግኘት መቻሉን ገልፀው በተጨማሪም የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ እየሆነ መሆኑንም አንስተዋል።
የጅኔላ ጤና ጣቢያ ሃላፊ መሀመድ አብራሂም በበኩላቸው ፤ ጤና ጣቢያው የተገልጋዮችን ዕርካታ ለማምጣት የጤና አገልግሎት ማሻሻያ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ለዚህም ከለውጡ ወዲህ የተሻለ የጤና ግብዓትና መድኃኒት እየቀረበና በተገልጋዩም ዘንድ ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎች እየተቀረፉ መሆኑን ተናግረዋል።
በጅኔላ ጤና ጣቢያ ለህክምና አገልግሎት መጥተው ያገኘናቸው ወይዘሮ ዘውዲቱ ለገሰ፤ በማህበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎት በመታቀፍ ህክምናቸውን እየተከታተሉ መሆኑን ተናግረዋል።
በጤና ተቋማቱም በቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፋ አገልግሎት ማገኘታቸውንም ገልጸዋል።
በጤና ተቋማቱ የመድኃኒት አቅርቦትን ጨምሮ የተሻለ ህክምና እያገኘን እንገኛለን ያሉት ደግሞ የሸንኮር ጤና ጣቢያ ተገልጋይ የሆኑት ወይዘሮ ፈቱሬ መኮንን ናቸው።