ቀጥታ፡

የመንገዱ መገንባት ቀደም ሲል ሲገጥመን የነበረን እንግልት አስቀርቶልናል - ነዋሪዎች

ቦንጋ፤ ግንቦት 11/2018 (ኢዜአ)፦ በአካባቢያቸው ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው መንገድ ቀደም ሲል ሲገጥማቸው የነበረውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ማስቀረቱን በኮንታ ዞን የኮንታ ኮይሻ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት በወረዳው የድልቢ ቀበሌ ነዋሪ አቶ በቀለ በተላ እና አቶ ብቸራ ቡሽራ ከዚህ ቀደም በአካባቢው መንገድ ባለመኖሩ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ለመንቀሳቀስ ይቸገሩ ነበር።


 

በመንገድ እጦት ሕሙማንንም ሆኑ ነፍሰጡር እናቶችን ወደ ሕክምና ተቋም ለማድረስ እንዲሁም የግብርና ምርታቸውን ለገበያ ለማቅረብ ይቸገሩ እንደነበርም አስታውሰዋል።

አሁን ላይ በአካባቢያቸው ተገንብቶ ለአገልግሎት የበቃው መንገድም ችግሩን መፍታቱን  ጠቁመዋል።

የመንገዱ ግንባታ ለፀጥታ ሥራ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ያነሱት ደግሞ ዋና ኢንስፔክተር ጊዲሶ አመሌ፣ በተለይ ችግሮች ሲከሰቱ  ፈጥኖ ቦታው ደርሶ ምላሽ ለመስጠት እንዳስቻለም  ተናግረዋል።

ወይዘሮ ጤናዬ ሹምቡል በበኩላቸው፤ የመንገዱ አገልግሎት መጀመር በተለይ ሴቶችና ተማሪዎች ላይ ሲገጥም የነበረን ችግር ማስቀረቱን ጠቁመው፣ ወላድ እናቶች ወደጤና ተቋማት ሄደው እንዲወልዱ ማስቻሉን ገልጸዋል።  

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ምክትል ሀላፊ ኢንጂነር ጌዲዮን እስጢፋኖስ፣ የክልሉ መንግስት የማህበረሰቡን የመንገድ መሰረተ ልማት ጥያቄዎች ለመመለስ ቀበሌን ከቀበሌ እና ከዋና መንገድ የማገናኘት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።


 

በዓለም ባንክ ድጋፍ የገጠር ትስስር ለምግብ ዋስትና ፕሮግራም በ6 ዞኖች ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች በ865 ሚሊዮን ብር የመንገድ ግንባታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል።

ሰሞኑን ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው የ12 ኪሎ ሜትር ደልባ-አልፋ-ቶልካ መንገድ ፕሮጀክት አንዱ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

መንገዱ ከሦስት በላይ ቀበሌዎችን እርስ በርስ የሚያገናኝና ከ52 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበትም ተናግረዋል።

የመንገዱ መገንባት ከዚህ ቀደም በአካባቢው ማህበረሰብ ላይ ይደርስ የነበረውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሌሎች ችግሮችን መፍታቱንም ኢንጂነር ጌድዮን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም