መቻል የሊጉን መሪነት ከሲዳማ ቡና መረከብ የሚያስችለውን ጨዋታ ከባህር ዳር ከተማ ጋር ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
መቻል የሊጉን መሪነት ከሲዳማ ቡና መረከብ የሚያስችለውን ጨዋታ ከባህር ዳር ከተማ ጋር ያደርጋል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 11/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 33ኛ ሳምንት ዛሬ በሚደረጉ ሶስት ጨዋታዎች ይጀመራል።
ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ባህር ዳር ከተማ ከመቻል በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ባህር ዳር ከተማ በ47 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል። ተጋጣሚው መቻል በ52 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በ32ኛ ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን 2 ለ 0 ያሸነፈው ባህር ዳር ከተማ በድል ጉዞው ለመቀጠል ይፋለማል።
በተመሳሳይ በ32ኛ ሳምንት ነገሌ አርሲን 4 ለ 0 የረታው መቻል ካሸነፈ ከሲዳማ ቡና በነጥብ እኩል በመሆን በግብ ክፍያ ብልጫ መሪነቱን ይረከባል።
ይህም በዋንጫ ፉክክሩ ወሳኝ የሚባል ምዕራፍ ይከፍታል።
በሌላኛው መርሐ ግብር ኢትዮጵያ መድን ከወላይታ ድቻ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የወቅቱ የሊጉ የዋንጫ ባለቤት ኢትዮጵያ መድን በ41 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ወላይታ ድቻ በ42 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል።
በ32ኛ ሳምንት ኢትዮጵያ መድን ከመቀሌ 70 እንደርታ አንድ አቻ ሲለያይ ወላይታ ድቻ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያደረገው ጨዋታ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
ጨዋታው ለሁለቱ ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ከመመለስ ባለፈ በወራጅ ቀጠና ስፍራ ከሚገኙ ክለቦች በነጥብ ለመራቅ ያስችላቸዋል።
ሀዲያ ሆሳዕና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
ባለፉት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ያሸነፈው ሀዲያ ሆሳዕና በ41 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተመሳሳይ 41 ነጥብ በግብ ክፍያ ብልጫ ወስዶ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በ32ኛ ሳምንት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሸገር ከተማን 2 ለ 1 ረቷል።
ሁለቱም ቡድኖች በድል ጉዟቸው ለመዝለቅ የሚያደርጉት ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 33ኛ ሳምንት እስከ ግንቦት 13 ቀን 2013 ዓ.ም ይቆያል። ሲዳማ ቡና በ55 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው።
የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን አቤል ያለው ከሲዳማ ቡና በ14 ጎሎች እየመራ ነው።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮቹ ናትናኤል ዳንኤል እና አዲስ ግደይ፣ የፋሲል ከነማው ታምራት ኢያሱ በተመሳሳይ 11 ግቦች ይከተላሉ።