ቀጥታ፡

ማንችስተር ሲቲ በዋንጫ ፉክክሩ የመቆየት ህልሙን ለማስቀጠል ከቦርንማውዝ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ተጠባቂ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 11/2018 (ኢዜአ)፦ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 37ኛ ሳምንት ዛሬ በሚደረጉ ጨዋታዎች ፍጻሜውን ያገኛል።

ምሽት 3 ሰዓት ከ30 ላይ ቦርንማውዝ ከማንችስተር ሲቲ የሚያደርጉት ጨዋታ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል።

ቦርንማውዝ በ55 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል። ማንችስተር ሲቲ በ77 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ቦርንማውዝ ባለፉት 16 የሊግ ግጥሚያዎች ሽንፈትን ሳያስተናግድ በአስደናቂ ግስጋሴ ላይ ይገኛል። 

ማንችስተር ሲቲ በዋንጫው ፉክክር ለመቆየት እና የሊጉን አሸናፊ በመጨረሻው ሳምንት እንዲወሰን ለማድረግ ከዛሬው ጨዋታ ሶስት ነጥብ መውሰድ ግድ ይለዋል።

ሲቲ ካሸነፈ ከሊጉ መሪ አርሰናል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት ዝቅ ያደርጋል።

ሻምፒዮንስ ሊግ የመግባት ተስፋ ያለው ቦርንማውዝ ለማንችስተር ሲቲ ጠንካራ ተፋላሚ እንደሚሆን ይጠበቃል።

በሌላኛው መርሐ ግብር ቼልሲ ከቶተንሃም ሆትስፐርስ ምሽት 4 ሰዓት ከ15 ላይ በስታምፎርድ ብሪጅ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ቼልሲ በ49 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል። ቶተንሃም ሆትስፐርስ በ38 ነጥብ 17ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በሊጉ የዓመቱን የመጨረሻ የሜዳ ጨዋታውን የሚያደርገው ቼልሲ ከሰባት የሊግ ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።

ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከጨዋታው አንድ ነጥብ ካገኘ በሊጉ መቆየቱን ያረጋግጣል።

በወራጅ ቀጠና የሚገኘው ዌስትሃም ዩናይትድ ትናንት በኒውካስትል ዩናይትድ 3 ለ 1 መሸነፉን ተከትሎ ስፐርስ በሊጉ የመቆየቱ እድል ይበልጥ ሰፍቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም