ቀጥታ፡

እውቀቶችን ከሰው ሰራሽ አስተውሎት ጋር በማጣመር የዲጂታል ሽግግሩን መደገፍ ይገባል 

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2018 (ኢዜአ)፦በስታቲስቲክስና ተያያዥ ዘርፎች ላይ ያሉ ባለሙያዎች እውቀታቸውን ከሰው ሰራሽ አስተውሎት መፍትሄዎች ጋር በማጣመር የዲጂታል ሽግግሩን በከፍተኛ ደረጃ ማገዝ ይገባል ተባለ።

''የመረጃ ሉዓላዊነት ለፖሊሲ ነፃነት'' በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው ሀገራዊ ጉባኤ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተካሂዷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)  ጉባኤውን በይፋ በከፈቱበት ወቅት እንዳሉት፤ መረጃ የዚህ ዘመን ስትራቴጂካዊ ሀብት እና ጠንካራ ሀገረ መንግሥት የሚገነባበት ቁልፍ የሉዓላዊነት ምሰሶ ነው።

በውጭ አካላት ላይ ጥገኛ የሆነ መረጃ ሀገራዊ መሻትን ማሳካት ስለማያስችል፣ የፖሊሲ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የራስን መረጃ በራስ አቅም መሰብሰብና መተንተን ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ይህ የመረጃ አሰባሰብና ትንተና ሥራ በሀገር ልጆች እውቀትና ክህሎት መከናወኑ ታላቅ ኩራት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ይህን ተከትሎ "የወደፊቱን መቅረጽ፦ ዲጂታሊ የተጠናከረ የስታቲስቲክስ ሥነ-ምህዳር" (Architecting the Future: A Digitally Fortified Statistical Ecosystem) በሚል መሪ ሀሳብ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።

በፓናሉ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሙሉቀን ቀሬ እንዳሉት፣ ስታቲስቲክስ በእውነትና በግምት መካከል ያለውን ክፍተት በሳይንሳዊ ዘዴ የሚያጠራ ጠንካራ መሳሪያ ነው።

ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሀገራዊ ክላውዶችን የገነባች ሲሆን፤ እነዚህን በማገናኘት የዳታ ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጥ የራስዋ ሉዓላዊ ክላውድ (Sovereign Cloud) እንዲኖራት እየተሰራ ይገኛል።

የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር)፤ በሀገሪቷ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞን ለማፋጠን የተቋማት መዋቅርና የሰለጠነ የሰው ኃይል ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሞዴሎችን ለማበልጸግና ቴክኖሎጂውን ስራ ላይ ለማዋል ጥራት ያለውና ወቅታዊ ዳታ መሰብሰብ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተው፤ ይህንን የሚያከናውን የተማረ የሰው ኃይል መገንባት ቀዳሚው ተግባር መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል።

በስታቲስቲክስና ተያያዥ ዘርፎች ላይ ያሉ ባለሙያዎች እውቀታቸውን ከሰው ሰራሽ አስተውሎት መፍትሄዎች ጋር በማጣመር የዲጂታል ሽግግሩን በከፍተኛ ደረጃ ማገዝ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

ለኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ትልቅ ፋይዳ ያለው እና በርካታ ችግሮችን የሚፈታ የአፍሪካ የመጀመሪያው የኤአይ ዩኒቨርሲቲ በአይቲ ፓርክ ውስጥ እየተገነባ ይገኛልም ብለዋል።

ሁሉም ዘርፎች የዲጂታልና የሰው ሰራሽ አስተውሎት ግብዓቶችን በደንብ በመውሰድና አሰራራቸውን በማጠናከር ዘርፋቸውን እንዲያሳድጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና ዳይሬክተር  ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ በበኩላቸው፤ የመንግስት የቴክኖሎጂ አካላት የሳይበር ደህንነትን (ሴኪውሪቲ) እና ፈጠራን  ጎን ለጎን በማስኬድ ሀገራዊ የዲጂታል ሽግግሩን ይበልጥ ደህንነቱ የተጠበቀ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ዘርፍ የነበራትን ዘግይቶ የመግባት ዕድል (Late-comer advantage) በመጠቀም በአሁኑ ወቅት የራሷን የዲጂታል መሪነት ሚና ማረጋገጥ መቻሏን ጠቁመዋል።

በቀጣዩ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ የመንግስት ተቋማትን እርስ በርስ በማስተሳሰር ሂደት ውስጥ የደህንነት ስርዓቶችን  የመገንባት ስራ በትኩረት እንደሚከናወን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሜሮን ከፈለው (ዶ/ር)፤ ተቋሙ የሚያመነጨው ማንኛውም የስታቲስቲክስ መረጃ  እውነተኛና ተዓማኒ መሆኑን በተግባር ማረጋገጥ መቻሉን ገልጸዋል።

ተቋሙ ያመረተው የዳታ ውጤት የሀገርን የዳታ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ትልቅ መተማመንን የፈጠረ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም