በሀገራት መካከል የሚፈጠር ጠንካራ የኢኮኖሚ ትስስር አስተማማኝና ዘላቂ መረጋጋትን ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው - ኢዜአ አማርኛ
በሀገራት መካከል የሚፈጠር ጠንካራ የኢኮኖሚ ትስስር አስተማማኝና ዘላቂ መረጋጋትን ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2018 (ኢዜአ)፦በሀገራት መካከል የሚፈጠር ጠንካራ የኢኮኖሚ ትስስር አስተማማኝና ዘላቂ መረጋጋትን ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው የጅቡቲ የኢኮኖሚ፣ ፋይናንስ፣ ኢንዱስትሪና ፕላኒንግ ሚኒስትር ኢልያስ ሙሳ ገለጹ።
በሶማሌ ክልል ርዕሰ መዲና ጅግጅጋ ከተማ በቀጣናው ሰላም እና ደኅንነት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ከፍተኛ ቀጣናዊ ፎረም እየተካሄደ ይገኛል።
’’ቀጣናዊ ተቋማትን ማጠናከር ለአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው ፎረም ቀጣናዊ መፍትሄዎች ለቀጣናዊ ችግሮች የሚለውን ዕሳቤ ማስተዋወቅ ዋና ዓላማው አድርጓል።
ይህ መድረክ በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት፣ በሰላም እና ፖለቲካዊ ምክክር ማዕከል፣ በሶማሌ ክልል መንግስትና ሌሎች አጋር አካላት በጋራ ተዘጋጅቷል።
በጅግጅጋ ከተማ በተዘጋጀው ፎረም ላይ የኢትዮጵያን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት መንግስታት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ምሁራን፣ ባለድርሻ አካላትና ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል።
የጅቡቲ የኢኮኖሚ፣ ፋይናንስ፣ ኢንዱስትሪና ፕላኒንግ ሚኒስትር ኢልያስ ሙሳ፤ ጅቡቲና ኢትዮጵያ ከፍተኛ የንግድ ትስስር ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አስታውሰው፤ በሀገራት መካከል የሚፈጠር ጠንካራ የኢኮኖሚ ትስስር አስተማማኝና ዘላቂ መረጋጋትን ለመፍጠር ትልቅ ማበረታቻ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ አካያ ለቀጣናዊ ብልፅግና እና ቀጣናዊ ሚዛንን ለመጠበቅ የኢትዮጵያ ሚና ታላቅ፣ ወሳኝና የማይተካ መሆኑን አክለዋል።
የቀጣናዊ ራዕዩ ዋና ማዕከል የኢኮኖሚ ትስስር እና የኢኮኖሚ ኮሪደሮች መሆን እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ በኃይል ትስስር ረገድ ያሳየችውን ታላቅ መሪነትና የተግባር አፈጻጸም ያደነቁት ሚኒስትሩ፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና የፋይበር ኦፕቲክ የቴሌኮም መሠረተ ልማቶች የሁለቱን ሀገራት ኢኮኖሚና ህዝቦች በማገናኘት ረገድ ያላቸውን ጉልህ ሚና ገልጸዋል።
በቀጣናው መጪው ጊዜ በጥንካሬ እንዲቃኝ፤ በጋራ ኃላፊነት፣ በኢነርጂ እንዲሁም በመሠረተ ልማት ትስስር ላይ የተመሰረተ ቀጠናዊ ትብብር መገንባት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ቀጣናው የጋራ ውሳኔዎችን የሚያሳልፍበትና በተግባር ላይ ያተኮረ ትብብር የሚያመነጭበት ጠንካራ መድረክ እንደሚያስፈልገው በማሳሰብ፥ ጅቡቲ በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት መካከል የሚደረጉ ውይይቶች ተቋማዊ ቅርፅ እንዲይዙ ሙሉ ድጋፏን እንደምትሰጥ አረጋግጠዋል።