ቀጥታ፡

የሥራ ፈጠራ ክህሎት ሥነ-ምህዳሩን ለማጠናከር የተዘረጉ የፖሊሲ ማዕቀፎች የፈጠራ ስራዎችን ለማሳደግ የጎላ ሚና እየተጫወቱ ነው 

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2018 (ኢዜአ)፦የሥራ ፈጠራ ክህሎት ሥነ-ምህዳሩን ለማጠናከር የተዘረጉ የፖሊሲ ማዕቀፎች የፈጠራ ስራዎችን ለማሳደግ የጎላ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።

የኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት (EDI) የሥራ ፈጠራ ባለሙያዎችንና አዳዲስ ፈጠራዎችን ለማበረታታት ያለመ በኢንስቲትዩቱ ግቢ "I Disrupt Hub" የተሰኘ ማዕከል አስመርቋል።


 

ማዕከሉን መርቀው የከፈቱት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለሐሳብና ለፈጠራ ተገቢው ክብርና እንክብካቤ እየተደረገ ይገኛል።

ይህ መሆኑም ሀገር በፈጠራ አቅሞች እንድትጠቀምና የማደግ ዕድሏ እንዲሰፋ ትልቅ በር እየከፈተ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የሥራ ፈጠራ ክህሎት ሥነ-ምህዳሩን ለማጠናከር የተዘረጉ እነዚህ የፖሊሲ ማዕቀፎች የፈጠራ ሥራዎችን ለማሳደግ የጎላ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በአሁኑ ወቅት እየተሰሩ ያሉ የፐብሊክ አንተርፕረነርሺፕ ሥራዎች በኮሌጆችና በኢንተርፕረነሮች ዘንድ ከፍተኛ መነቃቃትን እየፈጠሩ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ ይህም በፖሊሲ ኢኖቬሽን ላይ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት የተመረቀው ይህ ማዕከል የፈጠራ ሐሳቦችን ይበልጥ ለማፍለቅ የሚያስችል እና ዘርፉን በእጅጉ የሚያግዝ መሆኑንም ተናግረዋል።


 

የኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት (EDI) ዋና ዳይሬክተር ሐሰን ሁሴን (ዶ/ር) በበኩላቸው ፤ ላለፉት አምስት ዓመታት በተከናወኑት ዘርፈ-ብዙ ሥራዎች ሰዎች ህልማቸውን ለሀገርና ለወገኖቻቸው እንዲያካፍሉ እንዲሁም ሀብት መፍጠር እንዲችሉ ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል።

ወጣቶች ያላቸውን የፈጠራ አቅም ማገዝ፣ ድጋፍ ማድረግና እንቅፋቶቻቸውን በማስወገድ የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ ከግብ ማድረስ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም