ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በቁርጠኝነት እየሰራች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በቁርጠኝነት እየሰራች ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግስታት (ኢጋድ) የአየር ፀባይ ትንበያ ማዕከል ጋር በመተባበር 73ኛውን የምስራቅ አፍሪካ የአየር ፀባይ አዝማሚያ ትንተናና ትንበያ ፎረም በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በፎረሙ በአፍሪካ ቀንድ ከሰኔ እስከ መስከረም ድረስ የሚኖረው የአየር ንብረት ለውጥ ትንተናና ትንበያ ይቀርባል።
በፎረሙ የአገራት ምርጥ ተሞክሮዎች እንደሚቀርቡ ጠቁመው፤ ኢትዮጵያም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርን ጨምሮ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በወሰደቻቸው እርምጃዎች የተገኙ ውጤቶች የሚቀርቡበት ይሆናል ብለዋል፡፡
በአፍሪካ ቀንድ በሚስተዋለው ተደጋጋሚ ድርቅ፣ ጎርፍና የመሬት መንሸራተት ምክንያት ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው እንዲፈናቀሉና ለከፋ ጉዳት እንዲዳረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይህንን ቀጣናዊ ችግር በዘላቂነት ለመቋቋም ጥራት ያለውና ወቅታዊ የአየር ንብረት መረጃን ማጠናከርና ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኑንም አመልክተዋል።
በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) የሪዚሊየንስ ሀብ ኦፍ አፍሪካ ዳይሬክተር ዘይኑ ጀማል (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የአየር ንብረት ለውጥ ያደጉም ሆነ በማደግ ላይ ያሉ አገራት የጋራ ፈተና ሆኖ መገኘቱን ገልጸዋል።
በዚህም ምክንያት በሚከሰቱ የጎርፍ፣ የድርቅና የመሬት መንሸራተት አደጋዎች ዜጎች ለተለያዩ ችግሮች እየተዳረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለዚህ ችግር ፈጣን ምላሽ መስጠት የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም እገዛ ለማድረግ ሁሌም ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግስታት (ኢጋድ) ምክትል ዋና ጸሐፊ መሐመድ አብዲ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የአፍሪካ ቀንድ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ተደጋጋሚ አደጋ ከሚደርስባቸው የዓለም አካባቢዎች መካከል አንዱ ነው።
ይህንን አደጋ ለመከላከል የአገራት ቅንጅታዊ ስራ እንደሚያስፈልግ ተናግረው፤ ኢጋድም ችግሩን በዘላቂነት ለማቃለል ከአባል አገራትና ከዓለም አቀፍ የልማት ድርጅቶች ጋር ያለውን ትብብር እንደሚያጠናክር ጠቁመዋል።
በዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የቀጣናዊ ትብብር ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ኢሻም አባደር፤ በአፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በሚደረገው ርብርብ ድርጅታቸው በፋይናንስና በቴክኒክ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፦
በፎረሙ ላይ የቀጣናው አገራት ተወካዮች፣ የዘርፉ ባለሙያዎችና የዓለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች ተወካዮች የተገኙ ሲሆን፤ መድረኩ ነገም ቀጥሎ እንደሚውል ተገልጿል።