ቀጥታ፡

ዘላቂ ሰላም በማስፈን የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማረጋገጥ የቀጣናውን ተቋማት ቅንጅታዊ አሠራር ማጠናከር ይገባል 

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2018 (ኢዜአ)፦በምሥራቅ አፍሪካ ዘላቂ ሰላም በማስፈን የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማረጋገጥ የቀጣናውን ተቋማት ቅንጅታዊ አሠራር ማጠናከር እንደሚገባ በኬንያ የጋሪሳ ካውንቲ ግዛት ገዥ ናቲፍ ጃማ አደም ገለጹ።

በሶማሌ ክልል ርዕሰ መዲና ጅግጅጋ ከተማ በቀጣናው ሰላም እና ደኅንነት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ከፍተኛ ቀጣናዊ ፎረም እየተካሄደ ይገኛል።

’’ቀጣናዊ ተቋማትን ማጠናከር ለአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው ፎረም ቀጣናዊ መፍትሄዎች ለቀጣናዊ ችግሮች የሚለውን ዕሳቤ ማስተዋወቅ ዋና ዓላማው አድርጓል።

ይህ መድረክ በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት፣ በሰላም እና ፖለቲካዊ ምክክር ማዕከል፣ በሶማሌ ክልል መንግስትና ሌሎች አጋር አካላት በጋራ ተዘጋጅቷል።

በጅግጅጋ ከተማ በተዘጋጀው ፎረም ላይ የኢትዮጵያን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት መንግስታት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ምሁራን፣ ባለድርሻ አካላትና ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል።


 

የጋሪሳ ካውንቲ ግዛት ገዥ ናቲፍ ጃማ አደም በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የምክክር ፎረሙ ወቅታዊና እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፣ በምሥራቅ አፍሪካ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ቀጣናዊ ተቋማትን ማጠናከር ቀዳሚ ተግባር መሆን እንዳለበት ተናግረዋል። 

የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና በተለያዩ ተፈጥሯዊ ጸጋዎች የታደለ፣ ስትራቴጂካዊ መልክዓ-ምድር ያለው እንዲሁም አፍሪካን ከመካከለኛው ምሥራቅና እስያ ጋር የሚያገናኘው የዓለም ትልቁ የባህር ላይ ንግድ መስመር መገኛ መሆኑን ገልጸዋል።

ቀጣናው እምቅ የተፈጥሮ ሀብት፣ የበለጸገ ብዝኃ ባህልና ሰፊ የእንስሳት ሀብት ያለው ቢሆንም፤ ግጭት፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ድርቅና መፈናቀል ተደጋጋሚ ፈተናዎቹ ሆነው መቀጠላቸውን ገዥው ጠቁመዋል። 

ምሥራቅ አፍሪካ የዕውቀት፣ የተፈጥሮ ሀብት አልያም የአመራር እጥረት የለበትም ያሉት ናቲፍ ጃማ፤ በአሁኑ ወቅት የጎደለው የተቀናጀ የፖለቲካ አመራርና ቀጣናዊ እሳቤ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ይህንን ችግር ለማቃለል የአየር ንብረት ተጋላጭነትን በጋራ መከላከል፣ ድንበር ተሻጋሪ የአርብቶ አደሮችን እንቅስቃሴ በቅንጅት መምራት እና የቀጣናዊ መሠረተ ልማት ኮሪደርን ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል። 

በቀጣናው በአንድ ሀገር የሚከሰት ግጭትና አለመረጋጋት በቅጽበት በጎረቤት ሀገራት ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር የጠቀሱት ገዥው፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከንግግር የዘለለ የተቋማት መዋቅራዊ ትስስርና ቅንጅታዊ አሠራር መፍጠር እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም