ቀጥታ፡

ዩኒቨርሲቲው ምሩቃንን ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር ለማስተሳሰር በቅንጅት የጀመረውን ሥራ ያጠናክራል

ወልቂጤ፤ ግንቦት 10/2018 (ኢዜአ)፦ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የምሩቃንን የሥራ ክህሎት በማሳደግ ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር ለማስተሳሰር በቅንጅት የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው ምሩቃንን ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር በማስተሳሰር የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል"የሥራ አውደ ርዕይ" አካሂዷል።

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ሀብቴ ዱላ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ተቋሙ የገበያውን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ የትምህርት ፕሮግራሞችን በመክፈት ብቁና ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት እየሰራ ነው፡፡


 

ዩኒቨርሲቲው የምሩቃንን የሥራ ክህሎት በማሳደግ ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር የሚያገናኝ የሥራ አውደ ርዕይ ማዘጋጀቱንም ገልጸዋል፡፡

አውደ ርዕዩ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ መዘጋጀቱን ገልጸው፣ በዚህም ከ18 በላይ ቀጣሪ ድርጅቶች መሳተፋቸውንና 700 ለሚሆኑ ምሩቃን የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም መንግስት በአምራች ኢንዱስትሪው ላይ የጀመረውን የለውጥ ሥራ ውጤታማ እንደሚያደርግና የዩኒቨርሲቲ- ኢንዱስትሪ ትስስሩን እንደሚያጠናክር አመልክተዋል፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ኢንተርፕራይዝና ሥራ ዕድል ፈጠራ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ታምራት ተስፋሁን፤ ዩኒቨርሲቲው ተፈላጊ የትምህርት ፕሮግራሞችን በመክፈት የምሩቃንን የመቀጠር ምጣኔ እያሳደገ መሆኑን አንስተዋል።


 

በተያዘው ዓመትም በክልሉ 8 ሺህ 200 የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን በተለያዩ ተቋማት የሥራ ዕድል ማግኘታቸውን ጠቁመው፣ ተመራቂዎችን ከቀጣሪዎች ጋር ለማገናኘት የተጀመረው ተግባር የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡

የደስታ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ የሰው ሃይል አስተዳደር ሃላፊ አቶ ልሳነወርቅ ቦጋለ፤ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ያላቸውን ትስስር በማጠናከር ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቅሰዋል።


 

በተለያየ የሙያ መስክ የሰለጠኑ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንን ወደ ኢንዱስትሪው በማስገባት ጥራት ያለው ምርት በማምረት ተጠቃሚ ከመሆን ባሻገር ለዜጎች የሥራ ዕድል እየፈጠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የሥራ አውደ ርዕዩ ብቁና ተወዳዳሪ ምሩቃንን ለማግኘት ሰፊ ዕድል ይሰጣል ያሉት ደግሞ የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ባለሃብቶች ማህበር የክህሎት ልማት ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ማርታ ንጉሴ ናቸው፡፡


 

ባለፈው ዓመት ከሃዋሳና ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በተደረገው ትስስር 1ሺህ 700 ተመራቂዎች በፓርኩ የሥራ ዕድል ማግኘታቸውን አስታውሰዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የ5ኛ ዓመት የሶፍት ዌር ኢንጂነሪንግ ተማሪ ዓባይ አሸብር በበኩሉ፤ አውደ ርዕዩ ምሩቃንን ከቀጣሪዎች ጋር ለማገናኘት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግሯል፡፡


 

ይህም በተለይ ወጣቶችን ከቀጣሪ ድርጀቶች ጋር በማስተሳሰር የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ ስለሚፈጥር በቀጣይም መጠናከር አለበት ብሏል።

የሥራ አውደ ርዕዩ ምሩቃን ራሳቸውን ለቀጣሪ ድርጅቶች እንዲያስተዋውቁ ምቹ ሁኔታ የፈጠረላቸው መሆኑም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም