ቀጥታ፡

የአፍሪካ ቀንድ ትስስር በተግባር ያለ እውነት በመሆኑ ይበልጥ ሊጎለብት ይገባል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2018 (ኢዜአ)፦የአፍሪካ ቀንድ ትስስር በተግባር ያለ እውነት በመሆኑ በቀጣይ ተቋማዊና መዋቅራዊ መሠረተ ልማቶችን በመገንባት ይበልጥ ማጎልበት እንደሚገባ የሶማሊያ ፌዴራል ሪፐብሊክ የንግድ ሚኒስትር ጀማል መሐመድ ሀሰን ገለጹ፡፡  

በሶማሌ ክልል ርዕሰ መዲና ጅግጅጋ ከተማ በቀጣናው ሰላም እና ደኅንነት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ከፍተኛ ቀጣናዊ ፎረም እየተካሄደ ይገኛል።

’’ቀጣናዊ ተቋማትን ማጠናከር ለአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው ፎረም ቀጣናዊ መፍትሄዎች ለቀጣናዊ ችግሮች የሚለውን ዕሳቤ ማስተዋወቅ ዋና ዓላማው አድርጓል።


 

ይህ መድረክ በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት፣ በሰላም እና ፖለቲካዊ ምክክር ማዕከል፣ በሶማሌ ክልል መንግስትና ሌሎች አጋር አካላት በጋራ ተዘጋጅቷል።

በጅግጅጋ ከተማ በተዘጋጀው ፎረም ላይ የኢትዮጵያን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት መንግስታት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ምሁራን፣ ባለድርሻ አካላትና ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል።

የሶማሊያ ፌዴራል ሪፐብሊክ የንግድ ሚኒስትር አምባሳደር ጀማል መሐመድ ሀሰን ባደረጉት ንግግር፤ ቀጣናው ካለው ፈጣን የጂኦፖለቲካዊ ለውጦች አኳያ፣ ጥልቅ ስትራቴጂካዊ ትንተና በአስቸኳይ የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ መደረሱን አመልክተዋል። 

ስለ አፍሪካ ቀንድ የሚደረጉ ውይይቶች ሁል ጊዜም “በቀውስ ጊዜ አስተዳደር” ላይ ብቻ ከማተኮር መውጣት እንዳለባቸው ጠቅሰዋል፡፡

የቀጣናው ሕዝቦች ከዘመናዊ መንግሥታት መፈጠር በፊትም በንግድ የተሳሰሩ በመሆናቸው ትስስሩ ቀድሞውኑ በተግባር ያለ እውነት መሆኑን አስገንዝበዋል። 

የቀጣናው አገራት ሦስት መሰረታዊ ጉዳዮችን በፖሊሲ ማዕቀፍና ቅንጅት መመልከት እንዳለባቸው አመልክተው፤ አንደኛው በተበታተነ መልኩ ያለውን የንግድ አሰራር መቀነስና መቀናጀት እንደሚገባ ተናግረዋል።


 

በሁለተኝነት ያነሱት ነጥብ የድንበር አካባቢዎችን በመሰረተ ልማት በማስተሳሰር፣ የንግድ ልውውጥን በማጠናከር የዕድገት ሞተር አድርጎ መውሰድ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በሦስተኛ ደርጃ ትላልቅ የመሰረተ ልማት ዕቅዶችን ማለትም ወደቦችን፣ የትራንስፖርት ኮሪደሮችን፣ ዲጂታል ኔትወርኮችን እና የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ ግሪዶችን ከሀገር  ባለፈ መልኩ ለቀጣናው ትስስር እንዲሆን የማድረግ አስፈላጊነትን አብራርተዋል።

እነዚህ መሰረተ ልማቶች ምርታማነትን ያሳድጋሉ፣ የህዝብን መተማመን ያዳብራሉ፣ በማህበራዊ እድገት ላይ ቀጥተኛ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል በማለት ገልጸዋል።

ለዚህ ደግሞ የፖሊሲ ቀረጻዎች በውጭ ትንተና ላይ ብቻ ሳይደገፉ፣ የአገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት በነባራዊ እውነታዎች ላይ የተመሰረቱ ቀጣናዊ እውቀቶችን ማውጣት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

የአፍሪካ ቀንድ አባል ሀገራት ቀጣናዊ ትስስራቸውን በማጠናከር በታላላቅ የኢኮኖሚ ዕድሎችና ተስፋዎች እንዲታወቁ ማድረግ አስፈላጊነትን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም