በክልሉ ውጤታማ የተግባቦት ስራዎችን በማከናወን የህዝቡን የልማት ተሳትፎ የማጎልበት ሂደት ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ውጤታማ የተግባቦት ስራዎችን በማከናወን የህዝቡን የልማት ተሳትፎ የማጎልበት ሂደት ተጠናክሮ ይቀጥላል
ጋምቤላ ፤ ግንቦት 10/2018 (ኢዜአ)፦በጋምቤላ ክልል ውጤታማ የተግባቦት ስራዎችን በማከናወን የህዝቡን የልማት ተሳትፎ የማጎልበት ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ።
በክልሉ መንግስትና በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጀት ትብብር በውጤታማ ተግባቦትና በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዙሪያ ያተኮር የአቅም ግንባታ ስልጠና ለክልሉ አመራሮች ዛሬ በጋምቤላ ከተማ መሰጠት ተጀምሯል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሸኔ አስቲን፤ በስልጠናው ላይ እንደገለጹት ውጤታማ ተግባቦት የህዝቡን የልማት ተሳትፎ ለማጠናከር አይነተኛ ፋይዳ አለው።
ውጤታማ ተግባቦትን በማካሄድ የተጀመሩ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ስራዎችን ማሳለጥ እንደሚቻል አመልክተዋል።
ለዚህም አመራሩ በተግባቦት ጽንሰ ሃሳብ ዙሪያ የጠራ ግንዛቤ ሊይዝ እንደሚገባ ጠቁመው ስልጠናውም ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
አመራሩ ውጤታማ የተግባቦት ስራዎች በማከናወን ህዝቡን በልማቱ ለማሳለፍ በበለጠ ቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ስራዎችን ውጤታማ ለመድረግ እንዲሁም እንደ ሀገር የታለመውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ለማሳካት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በአቅም ግንባታ ስልጠናው ላይ ከክልል እስከ ወረዳ የሚገኙ አመራሮች እየተሳተፉ ነው።