በ460 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የዳዬ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በ460 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የዳዬ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ
ሀዋሳ፤ ግንቦት 10/2018 (ኢዜአ)፦በሲዳማ ክልል በ460 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የዳዬ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ።
በሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ እና በውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ (ዶ/ር) የተመረቀው የውሃ ፕሮጀክት ከ75 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተመላክቷል፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ መንግስት የህዝብን የልማት ጥያቄዎች በዘላቂነት ለመፍታት የሚያከናውናቸው ተግባራት ተጨባጭ ውጤት እየተገኘባቸው ነው።
የህዝብን ጥያቄዎች ለመመለስ በየደረጃው እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ፈጣንና አስተማማኝ ዕድገት ለማስመዝገብ በሚሰራው ሥራ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እየሆነ መጥቷል ብለዋል።
ዛሬ የተመረቀው የዳዬ ከተማ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የዚህ ማሳያ ነው ያሉት አቶ ደስታ፣ ልማቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የክልሉ መንግሥት የጀመረውን ስራ ያጠናክራል ሲሉ ገልጸዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት ፤ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወሳኝ በመሆኑ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
የዳዬ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ከ75ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግና ኢንቨስትመንትን ጨምሮ የአካባቢውን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን የሚያነቃቃ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የውሃ ፕሮጀክቱ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥ ነዋሪው ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ እንዲጠቀም አሳስበዋል።
የዳዬ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የነዋሪውን የረጅም ጊዜ ጥያቄ የፈታ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የሲዳማ ክልል ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ቢሮ ሀላፊ ኢንጂነር ከበደ ጋኖሌ ናቸው፡፡
ፕሮጀክቱ መንግሥት የነዋሪውን የልማት ጥያቄ በዘላቂነት ለመፍታት በጥናት የታገዘ ውጤታማ ሥራ እየሰራ ስለመሆኑ ማሳያ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የውሃ ፕሮጀክቱ 88 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ የውሃ መስመር ዝርጋታ የተደረገለት ሲሆን በሰከንድ 28 ሊትር የማመንጨት አቅም እንዳለውም ተገልጿል።
የውሃ ፕሮጀክቱ ከፌዴራል መንግሥት በተደረገ 460 ሚሊዮን ብር ድጋፍ እና በክልሉ መንግሥት ትብብር የተሰራ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና የሲዳማ ክልል ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።