ቀጥታ፡

የምስራቅ አፍሪካን ዘላቂ ሰላምና ዕድገት ለማፋጠን የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ትብብር ማጎልበት ያስፈልጋል 

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2018 (ኢዜአ)፦የምስራቅ አፍሪካን ዘላቂ ሰላምና ዕድገት ለማፋጠን የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ትብብር ማጎልበት እንደሚያስፈልግ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

በሶማሌ ክልል ርዕሰ መዲና ጅግጅጋ ከተማ በቀጣናው ሰላም እና ደኅንነት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ከፍተኛ ቀጣናዊ ፎረም እየተካሄደ ይገኛል።

’’ቀጣናዊ ተቋማትን ማጠናከር ለአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው ፎረም ቀጣናዊ መፍትሄዎች ለቀጣናዊ ችግሮች የሚለውን ዕሳቤ ማስተዋወቅ ዋና ዓላማው አድርጓል።

ይህ መድረክ በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት፣ በሰላም እና ፖለቲካዊ ምክክር ማዕከል፣ በሶማሌ ክልል መንግስትና ሌሎች አጋር አካላት በጋራ ተዘጋጅቷል።


 

በጅግጅጋ ከተማ በተዘጋጀው ፎረም ላይ የኢትዮጵያን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት መንግስታት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ምሁራን፣ ባለድርሻ አካላትና ተጋባዠ እንግዶች ታድመዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በፎረሙ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ፎረሙ የጋራ ዓላማን በማሳካት ሰላማዊና የተረጋጋ መፃኢ ጊዜን ለመቅረፅ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የአፍሪካ ቀንድ በዓለም ላይ ካሉ እጅግ አስፈላጊ ቀጣናዎች አንዱ ነው ያሉት አፈ ጉባኤ ታገሰ፤  ቀጣናውም የአህጉራት የገበያና ባህል ስትራቴጂካዊ ጥቅሞች ድልድይ ነው ብለዋል።

የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና መልክ ዓምድራዊ አቀማመጥና የህዝቦች ብዝኃ ትስስርም ከታሪኩ ጋር ተዳምሮ አስፈላጊነቱን እንዲጎላ ማድረጉን አስረድተዋል።

በሁሉም መለኪያ ወርቃማ ፀጋ የታደለው ቀጣናም ግጭት፣ አለመተማመን፣ መፈናቀል፣ የፖለቲካ ደካማነት፣ የሰብዓዊ መብት ጫና እና የውጭ ተፅዕኖ መታየት እንደሌለበት አብራርተዋል።


 

የአፍሪካ ቀንድ በችግርና ቀውስ መነጽር የሚታይበት አካሄድም ቀጣናውን ከትብብር ይልቅ የፉክክር መንደር ተደርጎ እንዲሳል ማድረጉን አንስተዋል።

ይህ መለወጥ አለበት ያሉት አፈ ጉባኤው፤ የአፍሪካ ቀንድ የወደፊት ዕጣ ፋንታም በራስ አቅም እንጂ በውጭ አካላት ሊጻፍ እንደማይገባ አስገንዝበዋል።

በዚህም የቀጣናውን ሀገራት ልማት፣ ሰላምና ደኅንነት ለማጠናከር የተቋማት፣ የማህበረሰቡ፣ የምሁራን፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሴቶችና ወጣቶችን ትብብር ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አፅንኦት ሰጥተዋል።

ቀጣናዊ ወኪልነትን ለማረጋገጥም በራስ ማሰብ፣ መፍትሔ መፈለግ፣ አጋርነትን ማጠናከር፣ የዕርስ በዕርስ ትብብርና የጋራ ዕድሎችን በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ዜጎች መቀረፅ እንዳለበት ገልጸዋል።

የምስራቅ አፍሪካ አጋሮችም ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ቀጣናዊ የልማት፣ ክብርና ሉዓላዊነት፣ ሰላምና ደኅንነትን የሚያረጋግጥ ድጋፍ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል።

ዘላቂ ሰላም በምኞት ብቻ አይገነባም ያሉት አፈ ጉባኤ ታገሰ፤ ሰላም የሚገነባውም በጠንካራ ተቋማት፣ በፍትሐዊና አካታች ትብብርና የፖለቲካ አጋርነት እንዲሁም በማይቋረጥ ውይይት ነው ብለዋል።

ሰላም በሕዝብ አመኔታና በተጠያቂ ተቋማት ላይ ሊመሠረት እንደሚገባ አፅንኦት የሰጡት አፈ ጉባዔው፤ ኢትዮጵያ ሰላማዊ፣ የተረጋጋና የተባበረ የአፍሪካ ቀንድ እንዲኖር ጥልቅ ፍላጎት እንዳላት አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ሰላም፣ ልማት፣ ትብብርና ቀጣናዊ ተሳትፎም ከጎረቤት ሀገራት ጋር የተሳሰረ መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህም የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ትብብርን በማጠናከር ሰላም ልማትና ብልፅግናቸውን ለማረጋገጥ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ አጋርነትን ማጎልበት እንዳለባቸው አንስተዋል።


 

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሐመድ፤ የሶማሌ ክልላዊ መንግስት ይህንን የጂግጂጋ ፎረም በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ብልጽግናን ለማስፈን የሚያስችሉ መንገዶችን ለመቀየስ የሚረዳ ስልታዊ የውይይት መድረክ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቀዋል።

ለረጅም ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ደህንነቱ ያልተጠበቀ አካባቢ ተደርጎ ይቆጠር የነበረው ክልል ዛሬ ተለውጦ እንዲህ አይነት የውይይት እና የሰላም ፎረም ማስተናገዱ ራሱ የሚሰጠው ተምሳሌትነት እጅግ የላቀ ትርጉም አለው ሲሉ ገልጸዋል።  

ይህ ታላቅ ውይይት በጂግጂጋ ከተማ መካሄዱ ልዩ ትርጉም እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም