በክልሉ ገበያን ለማረጋጋት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ገበያን ለማረጋጋት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ደብረ ማርቆስ፤ ግንቦት 10/2018 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል ገበያን ለማረጋጋት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑ ተመለከተ።
በደብረ ማርቆስ ከተማ ከ230 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ የተገነባ የገበያ ማእከል ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማእረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ ድረስ ሳሃሉ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ በክልሉ ገበያን ለማረጋጋት የሚያስችሉ ምርታማነትን የማሳደግ፣ የግብይት ስርአቱን የማሳለጥ፣ አምራችና ሸማቹን በቀጥታ የማገናኘትና ህገ ወጥ ደላሎች ላይ ቁጥጥር የማጠናከር ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
በደብረ ማርቆስ ከተማ የተገነባው የገበያ ማእከል የጥረቱ አንድ አካል መሆኑን ጠቁመው ማእከሉ አምራችና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት ግብይቱን በማሳለጥ በኩል ሚናው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር በዚህ በኩል እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይም አስተዳደሩ በዘርፉ ለሚያከናውናቸው ተግባራት ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ተሾመ ዋለ በበኩላቸው፤ የገበያ ማእከሉ አምራቹና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለመገበያየት የሚያስችል ነው ብለዋል።
ማእከሉ ለከተማዋ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑንም አስታውቀዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ ዮሴፍ መለሰ በበኩላቸው፤ የገበያ ማእከሉ ከ230 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ የተገነባ መሆኑን ተናግረዋል።
ማእከሉ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች የሚገበያዩበት በመሆኑ ለሸማቹ ህብረተሰብ የሚያስገኘው ጥቅም ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።
የገበያ ማእከሉ መገንባት የንግድ ስርአቱን ለማዘመን የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ያሉት ደግሞ የከተማው ንግድና ዘርፍ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሙሉጌታ አስረስ ናቸው።
በምረቃ ስነ ስርአቱ ላይ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።