ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በመደመር እሳቤ ቀጣናዊ አጋርነትን ለማጠናከር እየተጋች ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በመደመር እሳቤ በቀጣናው አብሮነትን በማጎልበት፣ ዘላቂ ሰላምንና ብልጽግናን በማረጋገጥ ቀጣናዊ አጋርነትን ለማጠናከር እየተጋች እንደምትገኝ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።

በቀጣናው ሰላም እና ደህንነት ላይ ትኩረቱን ያደረገውና “ቀጣናዊ ተቋማትን ማጠናከር ለአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ” በሚል መሪ ሐሳብ የተዘጋጀው ፎረም በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።


 

በፎረሙ መክፈቻ ላይ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ የፌደራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ከፍተኛ አመራሮች፣ የማህበረሰብ መሪዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የአፍሪካ ቀንድ የቀጣናውን የፖለቲካ፣ የጸጥታ እና የኢኮኖሚ ገጽታ የሚቀርጹ ውስብስብ እና እርስ በእርስ የተሳሰሩ ፈተናዎች የተጋረጡበት መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣናው የሚታዩት የድንበር ተሻጋሪ የጸጥታ ስጋቶች፣ ሕገወጥ ንግድ፣ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር እና ሌሎች የሽግግር ጊዜያዊ ስጋቶች ሰላምን የሚያደፈርሱና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን የሚያውኩ ናቸው ብለዋል።

እነዚህ ጫናዎች ተቋማዊ የቅንጅት ክፍተቶችን በማባባስ፣ ቀጣናው በጋራ ለመስራት እና ትርጉም ያለው የንግድና የኢኮኖሚ ትስስርን ወደ ፊት ለማራመድ ያለውን አቅም የሚገድቡ መሆናቸውን አብራርተዋል።

ለዚህም መሰል ቀጣናዊ የጋራ ፎረሞችን ማካሄድ ከፍተኛ ወሳኝነት እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡

ዘላቂ ሰላምና የጋራ ብልፅግና ሊመጣ የሚችለው መፍትሄዎች የህዝቡን ነባራዊ ሁኔታ፣ እሴት እና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች የሚያንፀባርቁ ሲሆኑ ብቻ ነው ብለዋል።


 

በመሆኑም ተግዳሮቶችን ለመሻገር፤ ሀገር በቀል ዕውቀትን፣ የአካባቢ ባለቤትነትን እና በዐውደ-ጽሑፍ ላይ የተመሰረተ ችግር መፍቻን ቅድሚያ የሚሰጠውን አዲስ አስተሳሰብ መቀበል እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሀገር ውስጥ መፍትሄዎችን በቁርጠኝነት በመምራት ረገድ መሪነት አሳይታለች ብለዋል፡፡

አካሄዳችን አገራዊ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች በመቅረጽ እና በአገር ውስጥ በመረጃ የተደገፈ ማሻሻያ ለማድረግ የዜጎች ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ ላይ ከፍተኛ ትኩረት የሰጠ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተተገበረው የመደመር እሳቤ መሰረት ኢትዮጵያ ተግባራዊ ያደረገቻቸው ሀገራዊ ሪፎርሞች የህዝቦችን ተጠቃሚነት ያረጋገጡና ሁሉን አቀፍ መሆናቸውን ገልጸው፤ ይህም የተለያዩ አቅሞችን በማሰባሰብ የተደመረ አቅምን የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህ አስተሳሰብ ቀጣናዊ አንድነትን በማጎልበት፣ ዘላቂ ሰላምን፣ ብልጽግናን እና ሰብዓዊ ክብርን በመደገፍ እውነተኛ ቀጣናዊ ትብብር እንዲኖር በማድረግ ዘላቂ አጋርነትን ያጠናክራል ብለዋል።

ኢትዮጵያ እየተከተለችው ያለው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ማሻሻያ ለሀገራዊ ልማት ስትራቴጂና ለቀጣናዊ ብልፅግና ያላትን ሰፊ ራዕይ የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።

ማሻሻያው የግሉን ዘርፍ በማነቃቃት ለሀገራዊ እድገት እና ለተረጋጋ የፋይናንስ አካሄድ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

እነዚህ ማሻሻያዎች የኢትዮጵያን የውስጥ ኢኮኖሚ ለመለወጥ ብቻ ሳይሆን፣ ለቀጣናዊ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ጠንካራ አስተዋፅኦ ለማድረግ ጭምር ያለሙ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ሥርዓትን ማዘመን፣ የመንገድና የባቡር መስመሮችን ማስፋፋት፣ የወደብ ተደራሽነትን ማሻሻል፣ እንዲሁም ከጎረቤቶቿና ከድንበር አካባቢዋ የሚያገናኙ የትራንስፖርት ኮሪደሮችን ማጠናከርን ጨምሮ ለመሠረተ ልማት ትስስር ቅድሚያ ሰጥታ እየሰራች ትገኛለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገትን ለመደገፍ እንዲሁም የአካባቢያዊ እና የአለም አቀፍ ገበያ ተደራሽነትን ለማሻሻል ንፁህ እና በተመጣጣኝ ዋጋ የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦትን በማስፋፋት የቀጣናውን የሃይል ፍላጎት በማሟላት ላይ ትገኛለች ብለዋል።

በጅግጅጋ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው ቀጣናዊ ፎረም እስከ ግንቦት 12 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም