ቀጥታ፡

በቀጣናው ዘላቂ ሰላምና ብልጽግናን ለማረጋገጥ ጠንካራ ትብብር ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፤ግንቦት 10/2018 (ኢዜአ)፡-በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምና ብልጽግናን ለማረጋገጥ ጠንካራ ቀጣናዊ ትብብር እንደሚያስፈልግ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) አስገነዘቡ።

በቀጣናው ሰላም እና ደኅንነት ላይ ያተኮረ ፎረም በጅግጅጋ ከተማ እየተካሄደ ነው።

ፎረሙ እየተካሄደ የሚገኘው “በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ቀጣናዊ ትስስርን ማጠናከር” በሚል መሪ ሐሳብ ነው።


 

ሚኒስትሩ በፎረሙ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ድንበር ተሻጋሪ የንግድና የኢኮኖሚ ትስስርን ማጠናከር የቀጣናችንን ውስብስብ የሰላምና ደኅንነት ፈተናዎች በዘላቂነት ለመፍታት ጉልኅ አስተዋጽዖ አለው ብለዋል።

አክለውም፤በተጠናከረ የተቋማት ቅንጅት ንግድን በማሳለጥ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትብብርን ለማጠናከር መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የቀጣናውን ዘመናት የተሻገሩ ችግሮች ለመፍታት የነበረውን የቅንጅት ክፍተት በመስበር፤ ነባራዊ ሁኔታን ያገናዘበና ትብብርን ማዕከል ያደረገ አዲስ የመፍትሔ አቅጣጫ መከተል እንደሚገባም አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ አካታች በሆነው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም፣ በመሠረተ-ልማትና የኃይል ትስስር እንዲሁም በአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናዊ ውኅደቱን ለማፋጠን በቁርጠኝነት እየሠራች እንደምትገኝም አረጋግጠዋል።

የቀጣናችን ሰላምና መረጋጋት የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ በመሆኑ፤በጋራ መተማመን ላይ የተመሰረተና ለተግዳሮት የማይበገር ቀጣናን ለመገንባት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትብብር እንዲሠሩ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምና ብልጽግናን ለማረጋገጥ ጠንካራ ቀጣናዊ ትብብር፣ የላቀ የኢኮኖሚ ውኅደት እና በሀገር በቀል ዕውቀት ላይ የተመሠረቱ መፍትሔዎች ሊተገበሩ እንደሚገባም አመላክተዋል።

የአፍሪካ ቀንድ እርስ በርስ የተሳሰሩ የፖለቲካ፣የጸጥታና የኢኮኖሚ ተግዳሮቶች ያሉበት መሆኑን በማስገንዘብ፤ ለዚህ ደግሞ የተቀናጀ ቀጣናዊ ምላሽ እንደሚያስፈልግ በአጽንኦት ገልጸዋል።


 

ድንበር ተሻጋሪ የጸጥታ እጦት፣አክራሪነት፣ ሕገ-ወጥ ንግድ እና የተቋማት ቅንጅት መላላት በቀጣናው ዘላቂ መረጋጋትና የኢኮኖሚ እድገት ላይ እያሳደሩት የመጣውን ተጽዕኖም አንስተዋል በንግግራቸው።

እንደ ዛሬው ፎረም ያሉ ተነሳሽነቶች በቀጣናው ዘላቂ ሰላምና ስትራቴጂካዊ ራስን የመቻል ዐቅምን ለመገንባት ለሚደረገው ውይይትና ትብብር ወሳኝ ዕድል እንደሚፈጥሩም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ የፖለቲካ፣የማኅበራዊ እና የኢኮኖሚ ተግዳሮቶችን ለመፍታት "ለሀገር በቀል መፍትሔዎች" የምትሰጠውን ትኩረት አረጋግጠው፤ለአብነትም በልዩነት ውስጥ አንድነትን እና የጋራ እድገት የሚያበረታታውን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቀረበውን የ“መደመር” ፍልስፍና ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ዋና ትኩረት የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ማጠናከር፣ምርታማነትን ማሻሻል እና በግል ዘርፍ የሚመራ እድገትን ማሳደግ መሆኑን በመጠቆም፤በተመሳሳይ ጊዜ ሀገሪቱን የቀጣናው የኢኮኖሚ ውኅደት አንቀሳቃሽ ኃይል ማድረግ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በትራንስፖርት ኮሪደሮች፣በሎጅስቲክስ ዘመናዊነት፣በባቡር መስመር ዝርጋታ እና በወደብ ተደራሽነት ማሻሻያ ላይ ያደረገችውን የመሠረተ-ልማት ኢንቨስትመንት ጠቅሰው፤ ይህም ለቀጣናዊ ውኅደት ያለውን የጎላ ፋይዳ አብራርተዋል።

በተጨማሪም ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ እድገትንና ቀጣናዊ ትስስርን ለመደገፍ ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ተመጣጣኝና ንጹህ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ረገድ እያደረገች ያለውን ቀጣናዊ የኃይል ኤክስፖርት ዕድገት አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምን፣ መረጋጋትን እና የኢኮኖሚ ትብብርን ለማስፈን ያላትን ቁርጠኝነትም አረጋግጠዋል።

ሰላማዊ፣የተቀናጀ እና በኢኮኖሚ ንቁ የሆነ ቀጣና ለመገንባት የጋራ መረዳዳት፣ የጋራ መተማመን እና ጠንካራ ቀጣናዊ አጋርነት አስፈላጊ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ፎረሙ እስከ ግንቦት 12 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ እንደሚቀጥል የወጣው መርሐ-ግብር ያስረዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም