ቀጥታ፡

የቀጣናው ዕጣ ፈንታ ላይነጣጠል የተሳሰረ ነው -ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) 

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2018 (ኢዜአ)፦የቀጣናው ዕጣ ፈንታ በማይነጣጠል መልኩ የተሳሰረ ነው ሲሉ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ገለጹ።

በቀጣናው ሰላም እና ደህንነት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ከፍተኛ ቀጣናዊ ፎረም በሶማሌ ክልል ርዕሰ መዲና ጅግጅጋ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡ 

ፎረሙ የሚካሄደው “ቀጣናዊ ተቋማትን ማጠናከር ለአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ” በሚል መሪ ሀሳብ ሲሆን፣ “ቀጣናዊ መፍትሄዎች ለቀጣናዊ ችግሮች” የሚለውን እሳቤ ማስተዋወቅ ዋና አላማው አድርጓል።


 

ይህ መድረክ በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት፣ በሰላም እና ፖለቲካዊ ምክክር ማዕከል (CRPP)፣ በሶማሌ ክልል መንግስት እና በሌሎች አጋር አካላት በጋራ የተዘጋጀ ነው። 

በፎረሙ መክፈቻ ላይ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ፣ የፌደራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ከፍተኛ አመራሮች እና የማህበረሰብ መሪዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። 

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፤ መድረኩ የውጭ ተዋናዮች ሳይገቡበት የቀጣናው አካላት በራሳቸው ጉዳይ፣ ፖሊሲና እርስ በእርስ ግንኙነት ላይ ብቻ የሚመክሩበት መሆኑን ገልጸዋል።

ቀጣናዊ እጣ ፈንታችን በጋራና በማይነጣጠል መልኩ የተሳሰረ ነው ሲሉም  አስገንዝበዋል።

ሁሉም አካል የሌላውን አዎንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖ መጋራቱ የማይቀር ነው ያሉት ዋና ጸሀፊው፤ ችግሮችን በጋራ መፍታት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በሞቃዲሾ፣ በአዲስ አበባ፣ በጅቡቲና በኬንያ ያሉ ማህበረሰቦች የእርስ በእርስ የአስተሳሰብና የእውነታ ክፍተት ሊኖርባቸው እንደሚችል የገለጹት ዋና ፀሐፊው፣ ይህ መድረክ ክፍተቱን ለመሙላት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህ ፎረም እርስ በእርስ ለመተዋወቅ፣ ግልፅነትን ለመፍጠርና ጠንካራ ትስስርን ለመገንባት የሚያስችል በመሆኑ በቀጣናው ያሉትን ግጭቶች ለመቀነስ በእጅጉ እንደሚረዳ አስገንዝበዋል።   

የአፍሪካ ቀንድ ፈተናዎች በቀጣናው ምሁራንና መሪዎች እጅ መፈታት እንዳለባቸው የጠቆሙት ዋና ፀሐፊው፣ ከማሕበራዊ ሚዲያ ፕሮፓጋንዳ ይልቅ እውነተኛውና ፍሬያማው መፍትሄ የሚገኘው በዚህ የውይይት መድረክ ላይ ነው ሲሉ ገልጸዋል። 

ይህ የጅግጅጋው ፎረም መሪዎችና ምሁራን ሁሉንም ሀሳቦች ይዘው በመምጣት በግልፅ የሚወያዩበት፣  የሚስማሙበት ወይም በልዩነቶች ላይ የሚግባቡበት መድረክ መሆኑን አብራርተዋል።


 

በመሆኑም በውይይቱ የሚገኙ ተጨባጭ ውጤቶችና መፍትሄዎች በቀጣይ ለሚቀረጸው የጋራ ጉዞ እጅግ ጠቃሚና መሰረታዊ ግብዓት እንደሚሆኑ አስገንዝበዋል።

ለኢጋድ እንደ ቀጣናዊ ተቋም የምሁራን ቡድን ውይይትና የውይይቱ ውጤት በቀጣይ አብሮ ለሚቀረጸው የጋራ ጉዞ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ጠቁመዋል። 

ይህ መድረክ ቀጣናው ፈተናዎች ተጨባጭ መፍትሄና አቅጣጫ የሚያስቀምጥ ጉባኤ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። 

ለዚህ ታላቅ ቀጣናዊ መድረክ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም