ቀጥታ፡

በአፍሪካ ቀንድ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለማለፍ የውይይት ባህልን ማጠናከር ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2018 (ኢዜአ)፦ በአፍሪካ ቀንድ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለማለፍ ለአካታች ውይይቶች መጠናከር ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ገለጹ።

በቀጣናው ሰላም እና ደህንነት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ፎረም በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።


 

ፎረሙ የሚካሄደው “ቀጣናዊ ተቋማትን ማጠናከር ለአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ” በሚል ሀሳብ ነው።

የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ(ዶ/ር) በፎረሙ ላይ እንደገለጹት በአፍሪካ ቀንድ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመሻገር ለአካታች ውይይት ቅድሚያ መስጠት እና ቀጣናዊ ህብረትን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

የሀገራቱ እጣፋንታ በጋራ የተሳሰረ መሆኑን የገለጹት ዋና ፀሐፊው፤ ምሁራን በጋራ በመሆን ወሳኝ ጉዳዮች ላይ መወያየት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የአፍሪካ ቀንድ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉ በሀገራቱ ቅንጅት መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያን፣ ሶማሊያን፣ ኬንያን፣ ጂቡቲንና ሌሎቹንም ሀገራት ያካተተ ውይይት በማድረግ በጋራ ጉዳዮች ላይ መተማመንን መፍጠር ይገባል ብለዋል።

ወርቅነህ ገበየሁ(ዶ/ር) ጠንካራ ኮሙኒኬሽንና ቀጣናዊ አካታችነትን ማጠናከርም የሚከሰቱ የሰላም ችግሮችን ለመፍታት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም