የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የጋራ አጀንዳችን ሆኖ ይቀጥላል-ተፎካካሪ ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የጋራ አጀንዳችን ሆኖ ይቀጥላል-ተፎካካሪ ፓርቲዎች
ባህር ዳር፤ግንቦት 10/2018 (ኢዜአ)፦የብሄራዊ ጥቅምና የሀገር ህልውና ጉዳይ የሆነው የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ በፅኑ አቋም የምንሰራበት የጋራ አጀንዳችን ሆኖ ይቀጥላል ሲሉ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።
ኢትዮጵያ የባህር መውጫ መግቢያ የተነፈጋት ሀገር ሆና መቀጠል የማትችልባቸው የተለያዩ አሳማኝ እውነታዎች ስለመኖራቸውም የፓርቲዎቹ አመራሮች አንስተዋል።
በአንድ ወቅት የባህር በር ባለቤት የነበረችው ኢትዮጵያ ምክንያቱ በውል በማይታወቅ ሁኔታ ከባህር እንድትርቅና የተቆለፈባት ሀገር እንድትሆን ተደርጓል።
ከቀይ ባህር በቅርብ ርቀት ላይ እያለች የኢፍትሃዊና ምክንያት አልባ በሆነ አግባብ ኢትዮጵያ ከባህር እንድትገለል የተደረገበት ጉዳይ የብዙ አመታት ቁጭት ቢሆንም አሁን ላይ ምላሽ የሚሻ የትውልድ ጥያቄ ሆኖ መጥቷል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የፖለቲካም ይሁን ሌላ ልዩነት ሳይገድበው በጋራ የቆምንለት የሀገር ህልውና ጉዳይ ነው ሲሉ የፓርቲ አመራሮች ተናግረዋል።
የአማራ ዲሞክራሲ ሃይሎች ንቅናቄ (አዴሃን) ስራ አስፈፃሚ አባል አዲሱ ጉልላት፤ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም ጉዳይ በተቃርኖ ሊቆም የሚችል የፖለቲካ አቋም መኖር እንደሌለበት የጸና እምነት አለን ሲሉ ገልጸዋል።
የሀገር ህልውና እና የብሄራዊ ጥቅም ጉዳይ የሆነው የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ መስራት የሁላችንም ግዴታ ነው ብለዋል።
በመሆኑም የሀገር ህልውና እና የብሄራዊ ጥቅም ጉዳይ የሆነው የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ መስራት የጋራ አጀንዳችን ሆኖ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ምክትል ሊቀመንበር መልካሙ ፀጋየ፤ ፓርቲያቸው በሀገር ብሄራዊ ጥቅም ጉዳይ ወደ ኋላ ሳይል እየሰራ መሆኑንና በቀጣይም አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር ያጣችበት ኢፍትሃዊነት ሁላችንም የምንቆጭበት በመሆኑ ለምላሹ ያለልዩነት በጋራ የምንሰራበት ታሪካዊ ምእራፍ ላይ እንገኛለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ በታሪክ፣ በመልክአ ምድርም ይሁን በዓለም አቀፍ ህግ ተቀባይነት ያለው ፍትሃዊ ጥያቄ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም የብሄራዊ ጥቅምና የሀገር ህልውና ጉዳይ የሆነው የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ በፅኑ አቋም የምንሰራበት የጋራ አጀንዳችን ሆኖ ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጰያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የሰሜን ኢትዮጵያ አስተባባሪ ሃይለማርያም ብርሃኑ፤ የባህር በር ለኢትዮጵያ አማራጭ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም ፓርቲያቸው ይህንን ሀገራዊ የህልውና ጉዳይ በፅኑ አቋም አጀንዳው አድርጎ የሚሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የብሄራዊ ጥቅምና የሀገር ህልውና ጉዳይ የሆነው የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ በዚህ ትውልድ ምላሽ ማግኘት ያለበት ብሄራዊ አጀንዳ መሆኑንም አጽኖት ሰጥተዋል።