የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚሰሩ ሥራዎች የአጋር አካላት ሚና የጎላ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚሰሩ ሥራዎች የአጋር አካላት ሚና የጎላ ነው
ጎንደር፤ ግንቦት 10/2018 (ኢዜአ)፦የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚሰሩ ሥራዎች የአጋር አካላት ሚና የጎላ መሆኑን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አስተዳደር ገለፀ።
የአማራ ልማት ማህበር (አልማ) በሰሜን፣ በምዕራብና በማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች በ186 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባቸውን የትምህርትና የጤና ተቋማት አጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ አድርጓል።
የልማት ማህበሩ በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ማክሰኚት ከተማ ያስገነባው አንድ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና የመማሪያ ክፍሎችን ነው ዛሬ ያስመረቀው።
በምረቃው ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አወቀ አስፈሬ፤ የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚሰሩ ሥራዎች የአጋር አካላት ሚና የጎላ መሆኑን አንስተዋል።
የአማራ ልማት ማህበር (አልማ) ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ሥራዎችን በማከናወን መንግስትን እያገዘና የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።
በማህበሩ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን ህዝቡ በገንዘብ፣ በቁሳቁስ፣ በጉልበቱና በእውቀቱ እንዲደግፍ የዞኑ መስተዳድር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።
በዞኑ በርካታ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ፣ ፍጥነትና ጥራት ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁም ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ነው ያስታወቁት።
በማህበሩ የጎንደር አካባቢ ልማት ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ዘውዴ እንደገለጹት፣ ማህበሩ በማህበራዊ ተቋማት ግንባታ ላይ አተኩሮ እየሰራ ነው።
በዘንድሮው ዓመት በ186 ሚሊዮን ብር ወጪ በሦስቱ ዞኖች ያስገነባቸው 38 የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸውን ገልጸዋል።
ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል ሁለቱ የጤና ኬላዎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ የቅድመ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን በ120 ሚሊዮን ብር ወጭ እየተገነቡ ያሉ 60 የትምህርትና የጤና ተቋማትን እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ለማጠናቀቅ ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
ማህበረሰቡ ለፕሮጀክቶቹ ግንባታ በጥሬ ገንዘብ 130 ሚሊዮን ብር አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመው፤ ተጨማሪ የአይነት፣ የጉልበትና የእውቀት አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል።
የማክሰኚት ከተማ ነዋሪው አቶ ጥበቡ ዘለቀ ፤ አልማ ለህዝብ የሚሰራ የህዝብ የልማት ተቋም ነው ብለዋል።
ልማት ማህበሩ በከተማው ለሚያስገነባቸው የትምህርት ተቋማት በገንዘብና በጉልበት በመደገፍ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
የልማት ማህበሩ በሰሜን፣ በምዕራብና በማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች ከ600 ሺህ በላይ አባላትን በማፍራት የተለያዩ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑም ታውቋል።