ቀጥታ፡

ለኒውክሊየር ኃይል ጣቢያ ግንባታ የሚሆን ምቹ አካባቢን በጥናት የመለየት ሥራ ተጀምሯል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2018 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ለኒውክሊየር ኃይል ጣቢያ ግንባታ ምቹ አካባቢን በጥናት የመለየት ሥራ እየተካሄደ መሆኑን የኢትዮጵያ ኒውክሊየር  ኃይል ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ከዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ (IAEA) ጋር በመተባበር ያዘጋጀውና በኒውክሊየር  ኃይል መገንቢያ ቦታ መስፈርቶችና ቅድመ ሁኔታዎች ላይ ትኩረት ያደረገ አውደ ጥናት እያካሄደ ይገኛል። 

ለአራት ቀናት በሚካሄደው በዚህ አውደ ጥናት ላይ ባለሙያዎችና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።


 

የኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሽፈራው ተሊላ በወቅቱ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ በሁሉም መስክ ያሉ እድገቶችን ቀጣይነት ለማረጋገጥ አስተማማኝ እና ዘላቂ የኃይል አቅርቦት ወሳኝ ነው። 

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በየዓመቱ 40 ቴራ ዋት አወር (TWh) ኃይል እንደሚያስፈልግ የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ በዚህም በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ውስጥ የኃይል ፍላጎቱ ወደ 77 ቴራ ዋት አወር ከፍ እንደሚል ጠቁመዋል።

በሀገሪቱ የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት፣ የዲጂታል መሰረተ ልማት እንዲሁም የአገልግሎት ዘርፉ እያደገ መምጣት ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት እንደሚጠይቅ ጠቅሰዋል፡፡

ይህንን የኃይል ፍላጎት በከፊል ከኒውክሊየር  ኃይል ለመሸፈን ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ጋር በመተባበር የኒውክሊየር  ኃይል ጣቢያ ለመገንባት የትኛው አካባቢ ምቹ እንደሆነ ለመለየት የሚያስችል ጥናት እያካሄደ መሆኑ ተገልጿል።

በአሁኑ ወቅት የዳሰሳ ጥናቱ እየተጠናቀቀ መሆኑን የገለጹት አቶ ሽፈራው፤ በቀጣይ ይበልጥ ዝርዝር ጥናቶች ተደርገው ግንባታው የሚካሄድበት ትክክለኛ ቦታ መረጣ ይከናወናል ብለዋል።


 

አሁን እየተካሄደ ያለው አውደ ጥናት ለቦታ መረጣው አስፈላጊ በሆኑ መስፈርቶችና አካሄዶች ላይ ጠቃሚ ግብዓት ለማግኘት እንደሚረዳም ጠቅሰዋል፡፡ 

በዘርፉ የሰው ኃይል አቅም ግንባታ እና አስፈላጊ የሕግ ማዕቀፎችን ሥራ ላይ ለማዋል የዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም አክለዋል፡፡ 

በዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ የኒውክሊየር ደህንነት ከፍተኛ ባለሙያ ሚካኤል ሳልሞን በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የኒውክሊየር ኃይልን ለእድገት ማቀላጠፊያ መሳሪያ ለማድረግ ህልም ሰንቃ ጉዞ መጀመሯ ትልቅ ውሳኔ ነው ብለዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ የኒውክሊየር ኃይል ግንባታ እቅድ እንዲሳካ ኤጀንሲው አስፈላጊውን የቴክኒክና የሙያ ድጋፍ ማድረጉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም