ቀጥታ፡

የደብረ ብርሃን ከተማን ለኢንዱስትሪ፣ ለኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ተመራጭ የማድረግ ተግባራት ይጠናከራሉ 

ደብረ ብርሃን ፤ ግንቦት 10/2018 (ኢዜአ)፦ የደብረ ብርሃን ከተማን ለኢንዱስትሪ፣ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ተመራጭ የማድረግ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የከተማዋ አስተዳደር ገለጸ።

የከተማዋ አስተዳደር የልማት ተነሺ ለሆኑ አርሶ አደሮች ልጆች የቤት መሥሪያ ቦታ በማስረከብ ለዘመናት ሲነሳ የነበረውን ጥያቄ መፍታት መጀመሩንም አስታውቋል።

የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት እንደገለፁት፤ የደብረ ብርሃን ከተማን ለኢንዱስትሪ፣ ለኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ተመራጭ የማድረግ ተግባራት ይጠናከራሉ።

የከተማዋን የመሬት ስሪት በማዘመን ከተማዋን ለሁለንተናዊ ልማት ተመራጭ የማድረግ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በዚህም በከተማዋ የተሳለጠ ልማትን እውን ለማድረግ ዘመናዊ የመሬት መረጃ አያያዝ ስርዓት ወደ ስራ መግባቱን  ገልጸው ነዋሪውም ከልማቱ ተጠቃሚ የሚሆንበት አሰራር እየተተገበረ መሆኑን አክለዋል። 

በዚህም ለአርሶ አደሩ ተገቢውን ካሳ በመክፈል መሬቱን ለልማት በማዋል የከተማዋ እድገት እንዲፋጠን በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

እድሜያቸው 18 ዓመትና ከዚያ በላይ ለሆኑ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች ልጆች የቤት መስሪያ ቦታ መስጠት በመቻሉ ለዘመናት ሲነሳ የነበረው የመልካም አስተዳደር ችግር መፈታቱን ጠቁመዋል።

የቤት መገንቢያ ቦታ የተሰጣቸው በ18 ማህበራት ለተደራጁ 431 የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች ልጆች መሆናቸውን አስረድተዋል።

ማህበራቱም በተረከቡት መሬት ላይ የከተማዋን ማስተር ፕላን በጠበቀ መልኩ የመኖሪያ ቤት ፈጥነው እንዲገነቡ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግም አረጋግጠዋል።

የከተማ አስተዳደሩ መሬት መምሪያ ሃላፊ እታለማሁ ይምታቱ በበኩላቸው የከተማዋን የመሬት መረጃ አያያዝ በማዘመን ለኢንዱስትሪ፣ ለንግድ፣ ለኢንቨስትመንትና ለመኖሪያ ቤት የማዋሉ ተግባር በትኩረት እየተከናወነ ነው ብለዋል።


 

የልማት ተነሺ ቤተሰቦች መሬታቸውን ለልማት በመልቀቅ ለከተማዋ እድገት መፋጠን አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ጠቁመዋል።

ቦታ ከተረከቡ የልማት ተነሺ ልጆች መካከል ላቀው ሙሉጌታ፤ አስተዳደሩ በልማት ምክንያት ከመሬታቸው የሚነሱ አርሶ አደሮች ልጆችን ማየት በመጀመሩ ደስተኛ ነኝ ብሏል።

በማህበር ተደራጅቶ 150 ሺህ ብር በመቆጠብ 150 ካሬ ሜትር የቤት መስሪያ ቦታ እንዳገኘም ወጣት ላቀው ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም