ቀጥታ፡

የፖሊሲ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የራስን መረጃ በራስ አቅም መሰብሰብና መተንተን ወሳኝ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2018 (ኢዜአ)፦ የፖሊሲ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የራስን መረጃ በራስ አቅም መሰብሰብ እና መተንተን ወሳኝ ግብዓት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ''የመረጃ ሉዓላዊነት ለፖሊሲ ነጻነት'' በተሰኘውና ኢትዮጵያ በመረጃና በስታቲስቲክስ የሉዓላዊነት ጉዞ ያስመዘገበችውን ትልቅ ድል በተበሰረበት ሀገራዊ ጉባኤና ኤግዚቢሽን ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ በዘርፉ የተመለከቱት እመርታ እጅግ አስደሳች ሆኖ እንዳገኙት ገልጸዋል።




መረጃ የዚህ ዘመን ስትራቴጂካዊ ሀብት እና ጠንካራ ሀገረ መንግሥት የሚገነባበት ቁልፍ የሉዓላዊነት ምሰሶ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

የተዋሰ አሊያም በውጭ አካላት ላይ ጥገኛ የሆነ መረጃ ሀገራዊ መሻታችንን ማሳካት ስለማያስችል፤ የፖሊሲ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የራስን መረጃ በራስ አቅም መሰብሰብ እና መተንተን ወሳኝ ግብዓት እንደሆነ አስገንዝበዋል።




ከሁሉም በላይ የመረጃ አሰባሰብና ትንተና ሥራ በሀገር ልጆች እውቀትና ክህሎት ሲከወን ማየት ታላቅ ሀገራዊ ኩራት መሆኑን በመልዕክታቸው አንስተዋል።

በተጨማሪም የመረጃ ትኩረታችን በቁጥር በሚገለጹ ውጤቶች ላይ ብቻ ሳይሆን ሰው ተኮር በሆኑና በዜጎች ሕይወት በሚታዩ ተጨባጭ ለውጦችም ላይ መሆን እንዳለበትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም