ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የተፈጥሮን ጉዳት እያከመ ለመሆኑ የሀሮማያ ሐይቅ ህያው ማሳያ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2018(ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የተፈጥሮን ጉዳት እያከመ ለመሆኑ የሀሮማያ ሐይቅ ህያው ማሳያ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የሀሮማያ ሐይቅ ዳግም መወለድ አረንጓዴ አሻራ ከሰጠን ፍሬዎች አንዱ ነው ብለዋል።


 

በ1996 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ ጠፍቶ የነበረው የሀሮማያ ሐይቅ፣ በአረንጓዴ አሻራ እና በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ጥረት ዛሬ ወደ ቀደመ ውበትና ሥሪቱ ተመልሷል ሲሉም ገልጸዋል።

ይህም አረንጓዴ አሻራን ለኢትዮጵያ የውሃ አካላትና ለተፋሰስ ልማት ቁልፍ ኢኒሼቲቭነቱን በተግባር ያረጋገጠ ነው ብለዋል።

ይህ ስኬት በመደመር እሳቤ ልማትን ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን፣ የተፈጥሮን ጫና መቋቋም እና መግራት እንደሚቻል ማረጋገጫ ነው ሲሉም አክለዋል።

በአካባቢው ስንደርስ ለተደረገልን አቀባበል ምስጋና አቀርባለሁ ነው ያሉት በመልዕክታቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም