ፓርቲው በለውጡ ዓመታት የተፈጥሮ ጸጋዎችን በማልማት ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ ውጤቶችን አስመዝግቧል - ኢዜአ አማርኛ
ፓርቲው በለውጡ ዓመታት የተፈጥሮ ጸጋዎችን በማልማት ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ ውጤቶችን አስመዝግቧል
አመያ፤ ግንቦት10/2018 (ኢዜአ)-ብልጽግና ፓርቲ በለውጡ ዓመታት እምቅ የተፈጥሮ ጸጋዎችን በማልማት በየዘርፉ ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ ውጤቶች ማስመዝገቡን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለጹ።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ኮንታ ዞን አመያ ከተማ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫን በማስመልከት የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳና የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደገለጹት በክልሉ ያሉ እምቅ የተፈጥሮ ጸጋዎች አልምቶ ጥቅም ላይ ለማዋል ባለፉት ዓመታት በፓርቲው መሪነት በተከናወኑ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል።
በፓርቲው የተነደፈው አገር በቀል የኢኮኖሚ እሳቤ በተለያዩ ዘርፎች እመርታዊ ስኬት ለማምጣት ማስቻሉንም ገልጸዋል።
የክልሉን ሕዝቦች የሠላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ በመመለስ ለሁለንተናዊ የብልጽግና ጉዞ መሰረት መጣሉንም ተናግረዋል።
በለውጡ ዓመታት ቀደም ሲል የተዘነጉ አካባቢዎችን ጭምር ፓርቲው የልማት ተጠቃሚ ማድረጉን ያመለከቱት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በዚህም የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት መሳደግ ተችሏል ብለዋል።
በቀጣይም ህዝብን ፍትሃዊ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች እንዲጠናከሩ፣ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫው ህብረተሰቡ ድምጹን ለፓርቲው በመስጠት ከጎኑ እንዲቆም ጠይቀዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የክልሉ ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ፍቅሬ አማን እንዳሉት፣ ፓርቲው ፈተናዎችን ተቋቁሞ በአካባቢ ያሉ ፀጋዎችን ወደልማት በመቀየር አኩሪ ድል እያስመዘገበ ይገኛል።
የክልሉ ህዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር ዴሞክራሲዊ ጥያቄም በለውጡ ዓመታት ምላሽ ማግኘቱን የገለጹት አቶ ፍቅሬ፣ የነበረው በክልል የመደራጀት ጥያቄ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በህዝቦች ንቁ ተሳትፎ እውን መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።
ብልጽግና የክልሉን ህዝብ የዘመናት የልማትና የማደግ ፍላጎት እውን ለማድረግ ፀጋዎችንና አቅሞችን አቀናጅቶ በመምራት መሰረታዊ ለውጥ ያመጣ ፓርቲ ነው ሲሉም ተናግረዋል ።
በቀጣይም ፓርቲው በጠቅላላ ምርጫው የህዝብ ይሁንታን ካገኘ ላልተመለሱ የህዝብ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ምላሽ ለመስጠት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠው፣ ለዚህም ህዝቡ ድምጹን በመስጠት ከጎኑ እንዲቆም ጠይቀዋል።
"ብልጽግና ፓርቲ ሁለንተናዊ እድገትን ለማረጋገጥ በትጋት እየሰራ ነው" ያሉት የኮንታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታከለ ተስፉ፣ በዞኑ ትኩረት የተነፈጋቸው የተፈጥሮ ሀብቶች በፓርቲው መሪነት በአዲስ እይታ ወደልማት ገብተው እመርታዊ ለውጥ መጥቷል ብለዋል።
ከዚህ ባለፈ ተጀምረው ያልተጠናቀቁና በይደር የቆዩ የመንገድ፣ የድልድይ፣ የውሃ፣ የጤናና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት መብቃታቸውን ነው የጠቀሱት።
ከሰልፉ ታዳሚዎች መካከል ወይዘሮ ውድነሽ ዶኖቾ እና ወጣት ሺባባው ሞገስ እንደገለጹት ብልፅግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት እንደሀገርም ሆነ እንደዞኑ በመሰረተልማት፣ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በቱሪዝም ዘርፎች የህዝብን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ በርካታ የልማት ሥራዎችን አከናውኗል።
በቀጣይም በፓርቲው መሪነት በሁሉም ዘርፎች የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ድጋፋቸውን ለመግለጽ በመርሀግብሩ ላይ እንደተገኙ ገልጸዋል።