ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ለሚመዘገበው ዕድገት መሠረት የሚሆን የሉዓላዊ ዲጂታል መሠረተ ልማት እየገነባች ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ለሚመዘገበው ዕድገት መሠረት የሚሆን የሉዓላዊ ዲጂታል መሠረተ ልማት እየገነባች መሆኑን የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) ገለጹ።

''የመረጃ ሉዓላዊነት ለፖሊሲ ነፃነት'' በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው ሀገራዊ ጉባኤ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በመካሄድ ላይ ነው።

በመድረኩ ማብራሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ለሚመዘገበው ዕድገት መሠረት የሚሆን የሉዓላዊ ዲጂታል መሠረተ ልማት እየገነባች ነው ብለዋል።

‎እንደ ግብርና፣ ጤና፣ ፋይናንስ፣ ትምህርት እና ኢነርጂ ያሉ እያንዳንዱ ዘርፎች አሁን ላይ በሀገር በቀል የክላውድ ቴክኖሎጂ የሚቀነባበሩ፣ በሀገር ውስጥ የሚመሩ እና በኢትዮጵያ ቋንቋዎች መግባባት ለሚችለው የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ግብዓት የሚሆኑ ተግባራዊ መረጃ ምንጮች ሆነዋል ነው ያሉት።

የራሳችን መረጃ ከሌለን የኛ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ባዕድ ይሆናል፤ የራሳችን አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ከሌለን ደግሞ መረጃዎቻችን ይባክናሉ ሲሉም አብራርተዋል።

‎"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ይህንን ክፍተት ለመሙላት የተቀረጸ ብሔራዊ ስትራቴጂ ሲሆን፤ ይህም ሉዓላዊ የክላውድ ዳታ ሴንተርን፣ ብሔራዊ የዳታ ሌክ ሀውስን እንዲሁም በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ፣ በትግርኛ እና በሶማሊኛ ቋንቋዎች የሰለጠነ እና ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ቁጥጥር ስር የሚመራ ሀገር በቀል ላርጅ ላንግዌጅ ሞዴልን መገንባትን ያካትታል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀዳሚ እየሆኑ ያሉት ሀገራት መረጃቸውን ወደ ምርታማነትና ወደ አዲስ የኢኮኖሚ እሴት እየቀየሩ ያሉ ናቸው፤ ኢትዮጵያም አሁን ላይ ይህንኑ መሠረት እየገነባች ትገኛለች ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም