ቀጥታ፡

ለቀጣናዊ ዘላቂ ልማት አስተማማኝና ወቅታዊ የአየር ንብረት መረጃ ማጠናከር ይገባል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2018(ኢዜአ)፦ለቀጣናዊ ዘላቂ ልማት ስኬት አስተማማኝ፣ ጥራት ያለውና ወቅታዊ የአየር ንብረት መረጃን በጋራ ማጠናከርና ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ ተናገሩ።    

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት( ኢጋድ) የአየር ጠባይ ትንበያ ማዕከል ጋር በመተባበር 73ኛውን የምስራቅ አፍሪካ የአየር ጸባይ አዝማሚያ ትንተናና ትንበያ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በፎረሙ ላይ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ተወካዮች፣ የዘርፉ ባለሙያዎችና የአለም ዓቀፍ ድርጅቶት ተወካዮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደች ትገኛለች።

የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና በአየር ንብረት መለዋወጥና ተያያዥ የተፈጥሮ አደጋዎች ተጋላጭ በመሆኑ፣ ይህንን ተፅዕኖ ለመቋቋም አስተማማኝ የመረጃ ልውውጥ ወሳኝ ነው ብለዋል። 

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ተፅዕኖ ለመቋቋም በርካታ አገራዊ ስራዎችን እያከናወነች እንደሚገኝም አብራርተዋል።

ከእርምጃዎች መካከል የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርንና የአየር ትንባያ ትንተናዎች የሚቲዎሮሎጂ ትንበያን ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገኙበት አንስተዋል።

በዚህም ተጨባጭ ለውጦች መመዝገባቸውን ነው የተናገሩት።

የአየር ትንበያ ትንተናዎችን ይበልጥ ትክክለኛና ተአማኒ ለማድረግ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን በጥቅም ላይ ማዋል መቻሉን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።

ለቀጠናዊ ዘላቂ ልማት አስተማማኝና ወቅታዊ የአየር ንብረት መረጃ ማጠናከር  እንደሚገባ አመላክተዋል።

የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና በተደጋጋሚ ለድርቅ፣ ለድንገተኛ ጎርፍና ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ መጋለጡ የጋራ ስጋት መሆኑ በፎረሙ ላይ ተነስቷል። 

በመሆኑም አገራቱ በየግል ከሚያደርጉት ጥረት ባለፈ፣ በቀጠና ደረጃ ወጥ የሆነና ሳይንሳዊ መረጃን መሰረት ያደረገ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራ ላይ ማዋል ይገባቸዋል ብለዋል።

የአየር ንብረት መረጃዎችን ማጠናከር አርሶ አደሮች፣ እንስሳት አርቢዎችና የፖሊሲ አውጪዎች አስቀድመው ውሳኔ እንዲያሳልፉና በልማት እቅዶች ላይ ዘላቂነት እንዲያረጋግጡ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ተገልፅዋል።

ፎረሙ ነገም ቀጥሎ እንደሚውል ተመላክቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም