ኢትዮጵያ የጥላቻ ንግግርና የተዛቡ መረጃዎችን ለመከላከል የሚደረገውን ቀጣናዊ ጥረት በግንባር ቀደምነት ትደግፋለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የጥላቻ ንግግርና የተዛቡ መረጃዎችን ለመከላከል የሚደረገውን ቀጣናዊ ጥረት በግንባር ቀደምነት ትደግፋለች
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2018 (ኢዜአ)፦ በዲጂታል ትስስር መስፋፋትና በሰው ሰራሽ አስተውሎ (AI) የሚታገዙ የጥላቻ ንግግሮችና የተዛቡ መረጃዎችን ለመከላከል በሚደረገው ቀጣናዊ ጥረት ኢትዮጵያ በግንባር ቀደምነት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኗን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍጹም ግርማ ገለጹ።
የምስራቅ አፍሪካ በይነ-መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የጥላቻ ንግግርንና ሀሰተኛ መረጃዎችን ለመከላከል ያዘጋጀው የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
የአፍሪካ ህብረት ተወካዮች፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢጋድ ከፍተኛ አመራሮች፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ)፣ የመከላከያ ሚኒስቴር፣ የመገናኛ ብዙኃን (ሚዲያ) እንዲሁም የሙያ ማህበራት ተወካዮች በመድረኩ ላይ ተገኝተዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ፍጹም ግርማ እንደገለጹት፤ የዲጂታል መድረኮች መስፋፋትና የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ መራቀቅ የጥላቻ ንግግሮችና የተዛቡ መረጃዎች ስጋትን ይበልጥ አጠናክሮታል።
ኢትዮጵያ ይህንን ስጋት ለመግታት አገራዊ እርምጃዎችን በግንባር ቀደምትነት መውሰዷን ጠቅሰው ፤ በተለይም በጥላቻ ንግግሮችና በሀሰት መረጃዎች ላይ ግልጽ የወንጀል ተጠያቂነትን የደነገገውን "የጥላቻ ንግግር እና የሀሰት መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ" በምሳሌነት አንስተዋል።
ሆኖም ግን አገር በቀል ጥረቶች ብቻቸውን በቂ እንዳልሆኑ ጠቁመው፤ የችግሩ ድንበር ተሻጋሪነት የጋራ ምላሽ የሚሻ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ድንበር ተሻጋሪ ስጋቶችን በብቸኝነት መከላከል ስለማይቻል የመንግስታት ትብብር፣ ቀጣናዊ ተቋማት፣ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ያካተተ የተቀናጀና ባለብዙ ወገን ምላሽ እንደሚያስፈልግ አፅንዖት ሰጥተዋል፡፡
ኢጋድ ይህንን የጋራ የመረጃ ስነ-ምህዳርን የማፅዳትና የቀጣናውን ሰላምና ማህበራዊ ትስስር የመጠበቅ ተነሳሽነት መውሰዱ የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከኢጋድ፣ ከአፍሪካ ህብረት፣ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ከሌሎች አጋሮች ጋር በመሆን ስጋቶቹን ለመቆጣጠርና የቀጣናውን ሰላምና ብልፅግና ለማረጋገጥ ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።
የኢጋድ የግጭት ቅድመ-ማስጠንቀቂያና ምላሽ መስጫ ዳይሬክተር ካልሙስ ኦሞንጎ በበኩላቸው፤ መድረኩ የሚመለከታቸው አካላት መረጃዎችን በተቀናጀ ሁኔታ የሚለዋወጡበት፣ በጋራ ወቅታዊ ሁኔታዎችን የሚገመግሙበትና ተያያዥ አደጋዎችን አስቀድመው የሚለዩበት ተግባራዊ የሥራ ትስስር እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
ይህም ማኅበረሰብን የሚከፋፍሉ መረጃዎች ከመሰራጨታቸው በፊት አስቀድሞ የመለየት እና ተገቢውን ሕጋዊና ሙያዊ ምላሽ የመስጠት ሂደትን ያቀናጃል ሲሉ አብራርተዋል።
የኢጋድ ሰላምና ደህንነት ዘርፍ ዳይሬክተር ኮማንደር አበበ ሙሉነህ በበኩላቸው፤ የጥላቻ ንግግሮችና የተዛቡ መረጃዎች ድንበር ተሻጋሪ ስጋቶች ስለሆኑ የሁሉም አገራት ትብብር ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
በተለይ የመገናኛ ብዙኃን አካላት ግጭትን በመከላከል፣ እውነታን በማረጋገጥና ኃላፊነትን በመጠየቅ ረገድ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አስታውቀዋል።
በመሆኑም ጋዜጠኞች መረጃዎችን በአግባቡ እንዲያረጋግጡ፣ አርታኢያን የዜና አቀራረብ ስልታቸውን በጥንቃቄ እንዲመርጡ እንዲሁም ተቋማት ደግሞ ግልጽና ወቅታዊ መረጃዎችን ለሚዲያ አካላት እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።
መድረኩ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ይሆናል።