ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ዲጂታል ሉዓላዊነት ከርዕይነት ባለፈ በተግባር ላይ ውሏል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዲጂታል ሉዓላዊነት አሁን ላይ ከርዕይነት ባለፈ በተግባር ላይ የዋለ መሠረተ ልማት ሆኗል ሲሉ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የዕቅድ ክትትልና ግምገማ ዲጂታላይዜሽን ዘርፍ ኃላፊ ዘሪሁን ከበደ ገለጹ።

''የመረጃ ሉዓላዊነት ለፖሊሲ ነፃነት'' በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው ሀገራዊ ጉባኤ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በመካሄድ ላይ ነው።

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የዕቅድ ክትትልና ግምገማ ዲጂታላይዜሽን ዘርፍ ኃላፊ ዘሪሁን ከበደ እንደገለፁት፤ የኢትዮጵያ ዲጂታል ሉዓላዊነት አሁን ላይ ከርዕይነት ባለፈ በተግባር ላይ የዋለ መሠረተ ልማት ሆኗል።

ይህ የዲጂታል ዕቅድ ክትትልና ግምገማ ሥርዓት እያንዳንዱን ብሔራዊ አመላካች፣ የሪፎርም ፕሮግራም እና የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን ቁልፍ የአፈጻጸም አመላካቾች በአንድ በተረጋገጠ ብሔራዊ መድረክ ላይ እንዲመሩ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

በዚህ ሥርዓት ውስጥ የሚገኘው አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በፌዴራልና በክልል ተቋማት ውስጥ ከሚገኙና ከጸደቁ ብሔራዊ መረጃዎች ላይ በመነሳት፣ የመረጃ ምንጮችን በመጥቀስ አሁናዊ ምላሾችን እንደሚሰጥ አመልክተዋል።

በመሆኑም የተበታተነ መረጃ እና የዘገየ ውሳኔ አሰጣጥ የነበረው የአመራር ፈተና አሁን ላይ ታሪክ ሆኗል ሲሉም ተናግረዋል።

‎ሥርዓቱ ተገንብቶ ተጠናቋል፤ የአመራርና የክትትል ማዕቀፉም ሥራ ላይ ውሏል፤ የተመዘገቡት ስኬቶችም ተጨባጭ እንደሆኑም ነው የገለጹት።

ይህም ለእያንዳንዱ ቁጥር አንድ የታመነ የመረጃ ምንጭ መኖርን፣ ሙሉ ተጠያቂነትንና የኦዲት ዐሻራን ከማረጋገጡም በላይ፣ አመራሩ ጊዜ ያለፈባቸው ሪፖርቶች ላይ ሳይሆን በወቅታዊ መረጃዎች ላይ ተመስርቶ ውሳኔ እንዲያስተላልፍ ማስቻሉን ተናግረዋል።

ቀጣዩ ምዕራፍ የእያንዳንዱ ተቋም ኃላፊነት ይሆናል፤ ይህም ከዚህ አንድ ወጥ ብሔራዊ ሥርዓት ጋር መገናኘት፣ ሥርዓቱን ተግባራዊ ማድረግ እና በዛም አማካኝነት መምራትን እንደሚያጠቃልል ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም