የመረጃ ሥርዓት ሪፎርሙ ፖሊሲዎች በማስረጃ ላይ እንዲመሠረቱና ተቋማዊ ተጠያቂነት እንዲሰፍን አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የመረጃ ሥርዓት ሪፎርሙ ፖሊሲዎች በማስረጃ ላይ እንዲመሠረቱና ተቋማዊ ተጠያቂነት እንዲሰፍን አድርጓል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2018 (ኢዜአ)፦ የመረጃ ሥርዓት ሪፎርሙ ፖሊሲዎች በማስረጃ ላይ እንዲመሠረቱና ተቋማዊ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ማድረጉን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ በረከት ፍስሃጽዮን አመለከቱ።
''የመረጃ ሉዓላዊነት ለፖሊሲ ነፃነት'' በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው ሀገራዊ ጉባኤ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት እየተካሄደ ይገኛል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ በረከት ፍስሃጽዮን በጉባኤው ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸው፤ የኢትዮጵያ የልማት አስተዳደር ሪፎርም ሀገሪቱ የምታቅድበትን፣ ክትትል የምታደርግበትንና ውጤት የምታስመዘግብበትን አካሄድ መሠረታዊ በሆነ መልኩ እየቀየረው እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ላለፉት በርካታ ዓመታት የተቀናጀ ሥርዓት አለመኖር፣ በእቅድና በፋይናንስ መካከል የነበረው ደካማ ትስስር እንዲሁም በሂደት ላይ ብቻ ያተኮሩ ሪፖርቶች ሀገራዊ ተጠያቂነትን አዳክመውት እንደነበር አስታውሰዋል።
ይህ ሪፎርም እነዚህን መዋቅራዊ ክፍተቶች በቀጥታ በመቅረፍ፤ ኢትዮጵያን ከመረጃ ማመንጨት ባለፈ መረጃን ጥቅም ላይ ለማዋል እንዲሁም የአፈጻጸም ተግባራትን በመረጃ ሳይደገፍ ከመመዝገብ ይልቅ ለዜጎች የመጡ ተጨባጭ ለውጦችን ለመለካት ወደሚያስችል ወሳኝ ምዕራፍ ማሸጋገሩን አመልክተዋል።
ዛሬ ላይ ከ113 በላይ የመንግሥት ተቋማት በአንድ ዕቅድ እና በአንድ ሪፖርት መርህ ላይ በተመሰረተ እንዲሁም ሙሉ በሙሉ በዲጂታል በተደገፈ የአፈጻጸም ክትትልና ግምገማ ሥርዓት ስር እንደሚሰሩም ነው ሚኒስትር ዴኤታው የጠቆሙት።
ሀገሪቱ ደረጃቸውን የጠበቁ ብሔራዊ የኢኮኖሚ ሂሳቦችን፣ የተናበበ የክልሎች አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርትን፣ ጠንካራ የህዝብ ኢንቨስትመን ማዕቀፍን እና ወቅታዊ አፈጻጸም ክትትልን ተግባራዊ በማድረግ የ10 ዓመቱን የልማት ዕቅድ ለማሳካት የሚያስችላትን ተቋማዊ ሉዓላዊነት እየገነባች እንደምትገኝም ገልጸዋል።
ይህም እያንዳንዱ የወጣ ገንዘብ ተጠያቂነት ያለው፣ እያንዳንዱ ፖሊሲ በማስረጃ ላይ የተደገፈ እና ለእያንዳንዱ ዜጋ ዋጋ ያለው መሆኑን ያረጋገጠ ነው ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው።