በኦሮሚያ ክልል 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የተፋሰስ ልማት ስራ ተከናውኗል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የተፋሰስ ልማት ስራ ተከናውኗል
አዳማ ፤ግንቦት 10/2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮ የበጋ ወቅት 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የተፋሰስ ልማት ስራ መከናወኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለፀ።
በቢሮው የደን ልማትና ተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ዳይሬክተር አቶ ከተማ አብዲሳ ለኢዜአ እንደገለፁት በክልሉ ባለፉት አመታት በተከናወነ የተፋሰስ ልማት ስራ የተራቆቱ አካባቢዎች አገግመዋል።
የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ እረገድም አበረታች ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
ተሞክሮውን አጠናክሮ በማስቀጠል በዘንድሮ በጋ ወቅት 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ልማቱ መካሄዱን ተናግረዋል።
በተፋሰስ ልማት ስራው የጋራና ማሳ ላይ እርከንና ክትር ጨምሮ የተለያዩ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል ።
የተፋሰስ ልማት ስራ በተከናወነባቸው ስፍራዎች ላይ በክረምት ወቅት የችግኝ ተከላ ለማካሄድ የጉድጓድ ቁፋሮና ሌሎች ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን አመልክተዋል።
በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተከናወነው የተፋሰስ ልማት ስራ የአፈር መሸርሸርና የጎርፍ ተጋላጭነትን በመቀነስ የመሬት ለምነት በመጨመሩ የግብርና ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ ማስቻሉን ጠቅሰዋል።
የተራቆቱ አካባቢዎች በማገገማቸው ለሰብል ልማት አመች የሆነ ዝናብና እርጥበት እንዲኖር ማስቻሉን ጠቁመው የገፀ ምድርና የከርሰምድር የውሃ ሀብት በመጨመሩም የመስኖ ልማት በስፋት እንዲካሄድ አመቺ ሁኔታ መፈጠሩን አመልክተዋል።
ባገገሙ ተፋሰሶች ላይ የእንስሳት መኖና የፍራፍሬ ልማት እንዲሁም የንብ ማነብ ስራዎች በማካሄድ ለስራ እድል ፈጠራ አይነተኛ ሚና መጫወቱንም ጠቅሰዋል ።
የደረቁ ወንዞች፣ ጅረቶችና ሃይቆች ተመልሰው ለሰውና እንስሳት መጠጥ ውሀ ምንጭነት እንዲሁም ለአሳ እርባታና ለሌሎች አገልግሎቶች እንዲውሉ በማስቻል እረገድ ከፍተኛ አስተዋጾ ማድረጉን አስታውቀዋል ።