በዩኒቨርሲቲው የሲቪል ሰርቪስ አሰራርና የሰው ሃይል ልማትን የሚያጠናክር ውጤታማ የምርምር ሥራዎችን እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዩኒቨርሲቲው የሲቪል ሰርቪስ አሰራርና የሰው ሃይል ልማትን የሚያጠናክር ውጤታማ የምርምር ሥራዎችን እየተከናወኑ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሲቪል ሰርቪስ አሰራርና የሰው ሃይል ልማትን የሚያጠናክር ውጤታማ የምርምር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የዩንቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ንጉስ ታደሰ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ 11ኛውን ዓመታዊ የምርምር ጉባኤ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ማካሄድ ጀምሯል።
ጉባኤው ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን በተለያዩ ምሁራን የጥናትና ምርምር ሥራዎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ተመላክቷል።
በዚሁ ጊዜ የዩንቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ንጉስ ታደሰ (ዶ/ር)፤ በተለያዩ መስኮች ብቁና የሰለጠነ የሰው ሃይል ማፍራት የሚያስችሉ የጥናትና ምርምር ውጤቶች እየፈለቁ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የሰለጠነ የሰው ሃይል የማፍራትና የተቋማትን አቅም የሚያጠናክር የምርምር ሥራዎችም የሲቪል ሰርቪስ አሰራርና የሰው ሃይል በማፍራት እየደገፈ መሆኑን ተናግረዋል።
11ኛው ዓመታዊ የምርምር ጉባኤም የሲቪል ሰርቪሱን ውጤታማነት ለማሻሻል ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ አንስተዋል።
በሁነቱ የሲቪል ሰርቪስ ሥርዓቱን የሚያዘምኑ የምርምር ውጤቶች ቀርበው ምክክር እንደሚደረግባቸው አስረድተዋል።
በጉባኤው የሚገኙ ውጤቶችና ባለድርሻ አካላት የሚሰጧቸው ግብዓቶች ተቀምረው ጥቅም ላይ እንዲውሉ እንደሚደረግ ገልጸዋል።