ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ብሔራዊ ስታቲስቲክስን የልማት ማዕከል በማድረግ የመረጃ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ እየሠራች ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ስታቲስቲክስን የልማት ማዕከል በማድረግ የመረጃ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ እየሠራች እንደምትገኝ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የኢኮኖሚ ስታቲስቲክስ ዘርፍ ኃላፊ አብዱልአዚዝ ሸፋ ገለጹ።

''የመረጃ ሉዓላዊነት ለፖሊሲ ነፃነት'' በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው ሀገራዊ ጉባኤ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት እየተካሄደ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የኢኮኖሚ ስታቲስቲክስ ዘርፍ ኃላፊ አብዱልአዚዝ ሸፋ በጉባኤው ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም ኢትዮጵያ ብሔራዊ ስታቲስቲክስን የልማት ማዕከል በማድረግ የመረጃ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሠራች መሆኑን አስገንዝበዋል።

በዚህም መሠረት፣ ተቋሙ ቀድሞ የነበረውን የወረቀት ላይ አሠራር በማስቀረት ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል የመረጃ አሰባሰብ መሸጋገሩን ጠቁመዋል።

ይህ ሽግግር የግብርና ቆጠራን እንዲሁም የስነ-ሕዝብና ጤና ጥናትን ዘመናዊ ለማድረግ ያስቻለ ሲሆን፣ በዘርፉ ላይ ከፍተኛ ውጤታማነትና ተጨባጭ ለውጥ ማስገኘቱንም ነው ያብራሩት።

እነዚህ ስኬቶች ከሀገሪቱ የዐሥር ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ፣ ከአፍሪካ ኅብረት የ2063 አጀንዳ እና ከዓለም አቀፉ የዘላቂ ልማት ግቦች ጋር የተናበቡ ሲሆን፣ የተቀረጹትም በጋራ ተሳትፎና ውህደት ላይ ተመስርቶ እንደሆነ አስረድተዋል።

ወደፊትም ሀገራዊ ልማታችን በመረጃ ላይ የተመሠረተና ሁሉን አቀፍ እንዲሆን ለማድረግ ሰፊ የሪፎርም ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አንስተዋል።

ከእነዚህም መካከል ፈጣንና ቀጥታ የመረጃ ሥርዓቶችን ማስፋፋት፣ የአስተዳደራዊ መዛግብትን ማቀናጀት፣ እንዲሁም በሰው ሠራሽ አስተውሎት፣ በሩቅ መረጃ ቅበላ እና በጂኦግራፊያዊ መረጃ ሥርዓት የሰው ኃይል አቅምን መገንባት ቀዳሚዎቹ ናቸው ብለዋል።

ይህ በመረጃ ዘርፍ የተመዘገበው ሀገራዊ ሽግግር ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ዕውቅና እንድታገኝ ያስቻላት ሲሆን፣ ተቋማዊ ተሞክሮዋን ለሌሎች ሀገራት ማካፈል የምትችል አርዓያ እንዳደረጋትም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም