ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ሰላምን በማስጠበቅ ህብረተሰቡን የልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግ የተሰራው ስራ ውጤታማ ነው

ሐይቅ፤ ግንቦት 10/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ሰላምን በማስጠበቅ ህብረተሰቡን የልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግ የተሰራው ስራ ውጤት ማስገኘቱን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) ገለፁ።


 

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በምረቃው እንደገለፁት፣ የክልሉን ሰላም በማጽናት በተለያዩ አካባቢዎች በርካታ የልማት ስራዎችን ማከናወን ተችሏል።

በዚህም እንደ ሐይቅ ከተማ ያሉ በርካታ የቱሪዝም፣ የግብርና እና ሌሎች ፀጋዎች ያሏቸው ከተሞች የብልጽግና ጉዞ መጀመራቸው የሚበረታታ ነው ብለዋል።

በከተማዋ በቅርቡ በገበታ ለትውልድ የተገነባው የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት በአጭር ጊዜ የከተማዋንና የአካባቢውን ገጽታ በመቀየር ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረጉን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በአጭር ጊዜ ተገንብቶ ዛሬ የተመረቀው የኮሪደር ልማት ለከተማው ቱሪዝም ተጨማሪ የመስህብ አቅምና ውበትን የፈጠረ ነው ብለዋል።

ህብረተሰቡ አንድነቱንና ሰላሙን በመጠበቅ የተጀመረውን ልማት በማስቀጠል ብልፅግናውን ለማረጋገጥ ከአካባቢው መስተዳድር ጋር ተባብሮ መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል።


 

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አሊ መኮነን፣ በበኩላቸው ህብረተሰቡን በማሳተፍ የዞኑን ሰላም ማስጠበቅ በመቻሉ ለልማት ስራዎች ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል።

በዞኑ የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተገነቡና እየተመረቁ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ጠቁመው በሐይቅ ከተማ ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው የኮሪደር ልማት የዚሁ ማሳያ ነው ያሉት።

የኮሪደር ልማቱ ከሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ጋር ተደምሮ ለከተማዋ ተጨማሪ ውበትን የፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው ይህም ምቹ የመኖሪያ አካባቢን ለመፍጠርና ጎብኚዎችን ለመሳብ ያስችላል ብለዋል።


 

የሐይቅ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ከድር መሀመድ በበኩላቸው፣ በከተማው በ130 ሚሊየን ብር የተገነባው ኮሪደር ልማት በአጭር ጊዜ በጥራት ተጠናቆ ለምረቃ መብቃቱን ተናግረዋል።

የኮሪደር ልማቱ የእግረኛና የሳይክል መንገድን ጨምሮ ሌሎችንም የመዝናኛ ስፍራዎች ያካተተ መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም