ሀገራዊ ምክክሩ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር የሃላባ የባህል ሽማግሌዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር የሃላባ የባህል ሽማግሌዎች ገለጹ
ሀላባ፣ ግንቦት 10/2018 (ኢዜአ)፡-ሀገራዊ ምክክሩ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥና ለችግሮች መፍትሄ ለመስጠት ትልቅ አቅም እንደሚሆን የሃላባ የባህል ሽማግሌዎች ገለጹ።
ለምክክሩ ስኬታማነት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
ለኢትዮጵያ የዜና አገልግሎት አስተያየታቸውን ከሰጡት የባህል ሽማግሌዎች መካከል ሀጂ ገራድ ድልታታ ሙዜ ሀገራዊ ምክክሩ የአብሮነት እሴትን በማጠናከር በጋራ ለመልማት በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።
ለዚህም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት የጀመረውን ጥረት መደገፍ ይገባል ብለዋል።
የተሻለች ሃገርን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ የሃላባን የሽምግልና ሥርዓቶች በግብዓትነት በመጠቀም ለምክክሩ ስኬት እገዛ እያደረጉ መሆናቸውንም አንስተዋል።
ትውልዱ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶችን ለሃገር እድገት እንዲያውል የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑንም አክለዋል።
ምክክር ለሃገር ሰላምና ልማት መጠናከር ወሳኝ ነው ያሉት ደግሞ ሌላው የሀላባ ባህል ሽማግሌ ገራድ ሙንዲኖ ሁሴን ናቸው።
በሃላባ ባህል ችግሮችን በመመካከር የመፍታት ልምድን በመጠቀም ለአካባቢው ሰላምና አብሮነትን ለማጠናከር እየሰሩ መሆናቸውን የገለጹት ገራድ ሙንዲኖ፣ በሀገራዊ ምክክሩ አጃንዳዎችን በማቅረብ የበኩላቸውን አስተዋጾ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።
ኢማም ሽኩራላ ሃጂ መሀመድ በበኩላቸው፣ እንደ ሃገር አለመግባባቶችን በምክክር ለመፍታት የተጀመረውን ጥረት በማሳካት ረገድ የበኩሌን እየተወጣሁ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ለምክክሩ ስኬታማነት ልዩነቶችን በሰለጠነ መንገድ ተነጋግሮ በማጥበብ ለሃገር ሰላምና እድገት በጋራ መስራት ይገባል ሲሉም መክረዋል።