በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሚመራ ሉዓላዊ የዲጂታል ኢንተለጀንስ መሠረተ-ልማት እየተገነባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሚመራ ሉዓላዊ የዲጂታል ኢንተለጀንስ መሠረተ-ልማት እየተገነባ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2018 (ኢዜአ)፦ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሚመራ ሉዓላዊ የዲጂታል ኢንተለጀንስ መሠረተ-ልማት እየተገነባ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሜሮን ከፈለው (ዶ/ር) ገለጹ።
''የመረጃ ሉዓላዊነት ለፖሊሲ ነፃነት'' በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው ሀገራዊ ጉባኤ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት እየተካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሜሮን ከፈለው (ዶ/ር) የሀገሪቱ ብሔራዊ የስታቲስቲክስ ሥርዓት ስላደረገው የዲጂታል አሰራር ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ተቋሙ ከተበታተነ እና በእጅና በወረቀት ከሚሠራ አሠራር ወጥቶ፤ በኮምፒውተር የታገዘ የግል ቃለ-መጠይቅ ሥርዓት፣ የጂኦግራፊያዊ መረጃ ሥርዓት ውህደት፣ የሪሞት ሰንሲንግ፣ የክላውድ መሠረተ-ልማት፣ እንዲሁም ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (ኢንሳ) ጋር በመተባበር በሀገር ውስጥ የቆጣሪዎች መከታተያ መድረክን በመጠቀም ወደ ሙሉ ዲጂታል እና ቅጽበታዊ (Real-time) የስታቲስቲክስ ሥነ-ምህዳር መሸጋገሩን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ላይ መረጃ በመሰብሰብ ላይ ብቻ እንዳልተወሰነች፤ ይልቁንም 26 በሀገር አቀፍ ደረጃ የተገናኙ ቅርንጫፎችን፣ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) የሚመራ የጥናትና ቆጠራ የመረጃ ቋት፣ እንዲሁም በዘመናዊ መሠረተ-ልማት እምነት በሚጣልባቸው ስልቶች እና ብቃት ባለው የኢትዮጵያውያን የሰው ኃይል ላይ የተመሠረተ ግልጽ የፍኖተ ካርታ የያዘ ሉዓላዊ የዲጂታል ኢንተለጀንስ መሠረተ-ልማት እየገነባች መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል።