ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ ልማት ፕሮግራም ሥር ታላላቅ ሀገራዊ ስኬቶች ተመዝግበዋል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ ልማት ፕሮግራም ሥር ታላላቅ ሀገራዊ ስኬቶች መመዝገባቸውን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ትንተና ቢሮ ኃላፊ አባስ መሐመድ ገለጹ።

''የመረጃ ሉዓላዊነት ለፖሊሲ ነፃነት'' በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው ሀገራዊ ጉባኤ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት እየተካሄደ ነው።

በፕላንና ልማት ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ትንተና ቢሮ ኃላፊው አባስ መሐመድ፣ ስለ ኢትዮጵያ የመረጃ ሉዓላዊነት ጉዞ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም ሕጋዊ ዕውቅና ያላቸው፣ በሳይንሳዊ ስልት የተዘጋጁ እና ለሕዝብ ክፍት የሆኑ ይፋዊ ስታቲስቲክስ እንዴት ጥሬ መረጃዎችን ወደ ተጨባጭ ማስረጃ፣ ማስረጃዎችን ደግሞ ወደ መልካም አስተዳደር እንደሚቀይሩ ገልጸዋል።

ያለ መረጃ የሚታቀድ ትልም ምኞት ብቻ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው፤ የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የአሥር ዓመቱ የልማት ዕቅድ እምነት የሚጣልባቸውና የኢትዮጵያውያን ባለቤትነት የተረጋገጠባቸውን መረጃዎች (ቁጥሮች) እንደሚሹ ተናግረዋል።

‎በተጨማሪም በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ ልማት ፕሮግራም ሥር የተመዘገቡ ታላላቅ ስኬቶችን አጉልተው ያሳዩ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሙሉ በሙሉ ይፋ የተደረገውን የሥነ-ህዝብ እና ጤና ጥናት፣ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን የመንግሥት ሠራተኛ ባለሙያዎች የተከናወነውንና ከተለመደው ያደገውን የተቀናጀ የቤተሰብ ጥናት፣ እንዲሁም በግብርና ቆጠራ እና በኢኮኖሚ ተቋማት ቆጠራ ላይ የተመዘገቡ ዋና ዋና እመርታዎችን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም