በኦሮሚያ ክልል በመኸር እርሻው 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት በሩዝ ሰብል ይለማል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል በመኸር እርሻው 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት በሩዝ ሰብል ይለማል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በተያዘው የመኸር እርሻ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት በሩዝ ሰብል እንደሚለማ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ በሪሶ ፈይሳ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ክልሉ ለሩዝ ልማት ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በተሠራው ሥራ ተጨባጭ ውጤት እየታየ ነው።
በክልሉ በ2014/15 የምርት ዘመን በ100 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ተጀምሮ የነበረው የሩዝ ልማት፣ አሁን ላይ በከፍተኛ ሁኔታ በማደግ የሕዝቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ይገኛል ብለዋል።
ይህ የሩዝ ልማት በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ በሚገኙ ዞኖች በስፋት እየለማ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።
ባለፈው ዓመት 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ ከለማው የሩዝ ሰብል ወደ 63 ሚሊየን ኩንታል ምርት መገኘቱን ጠቁመው በ2018/19 የምርት ዘመን 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት በማልማት 100 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዷል ብለዋል።
በክልሉ በሩዝ ልማት ውጤታማ ለመሆን አመቺ የሆኑ አካባቢዎች በጥናት ተለይተው ኢኒሼቲቩ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት።
አሁን ላይ ለአርሶ አደሩ የሚያስፈልገው ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በበቂ ሁኔታ የቀረበ ሲሆን፤ የባለሙያ የቅርብ ድጋፍና ክትትልም እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ከሩዝ ልማቱ አምራች አርሶ አደሮች የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ፣ ምርቱን ለገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መጥቷል ብለዋል።
በልማቱ ዙሪያ የአርሶ አደሩ ተነሳሽነት በየጊዜው እያደገ የመጣ ሲሆን፤ ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሰፋና አርሶ አደሩም በሩዝ ልማት ላይ የተሻለ ልምድ እያገኘ መሆኑን ገልጸዋል።