ቀጥታ፡

በመንግስት በተወሰዱ ቁርጠኛ እርምጃዎች የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የፖሊሲ ነፃነት የሚያረጋግጥ የመረጃ ሥርዓት መገንባት ተችሏል - ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2018 (ኢዜአ)፦ መንግስት በወሰዳቸው ቁርጠኛ እርምጃዎች የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የፖሊሲ ነፃነት የሚያረጋግጥ የመረጃ ሥርዓት መገንባት መቻሉን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ።

''የመረጃ ሉዓላዊነት ለፖሊሲ ነፃነት'' በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው ሀገራዊ ጉባኤ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት እየተካሄደ ይገኛል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በጉባኤው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ቀደም ሲል ሀገራዊ የመረጃ ሥርዓቱ በራስ አቅም ላይ ያልተመሠረተ በውጭ ድጋፍ ጥገኝነት ላይ የቆየና የተዓማኒነት ጥያቄዎች የሚነሱበት እንደነበር አንስተዋል።

‎ከዚህ ለመላቀቅ በተደረጉ ቁርጠኛ እርምጃዎች የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርምና የ10 ዓመቱን የልማት ዕቅድ አፈጻጸም መከታተል የሚያስችሉ እንደ የተቀናጀ የቤተሰብ ጥናት፣ የቱሪዝም መረጃ እና የቢዝነስ ድርጅቶች ቆጠራ ያሉ የተለያዩ የዳሰሳ ጥናት በማድረግና በዲጂታል ሥርዓት በማዘመን እንዲሁም ለመረጃ ልማት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በማድረግ የመደመር እሳቤን መሠረት ያደረገ የመረጃ ተኮር ፖሊሲ አመራርና ውሳኔ ሰጪነትን ማረጋገጥ መቻሉን አመልክተዋል።

‎ይህ ዓይነቱ የሪፎርም ውጤት፤ መረጃዎች በኢትዮጵያ ልጆች እንዲሰበሰቡና እንዲተነተኑ በማድረግ የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የፖሊሲ ነፃነት የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

ብሔራዊ ጥቅምን፣ የዜጎችን ደኅንነትና የልማት ትልሞችን በጽኑ መሠረት ላይ በመገንባት ከተለመደው የምላሽ ሰጭነት አሠራር ወደ ቅድመ-ትንበያ መሸጋገር የሚያስችል ዘላቂ ተቋማዊ ዐቅም መፈጠሩን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም