''የመረጃ ሉዓላዊነት ለፖሊሲ ነፃነት'' በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ ሀገራዊ ጉባኤ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
''የመረጃ ሉዓላዊነት ለፖሊሲ ነፃነት'' በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ ሀገራዊ ጉባኤ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2018 (ኢዜአ)፦ ''የመረጃ ሉዓላዊነት ለፖሊሲ ነፃነት'' በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው ሀገራዊ ጉባኤ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት እየተካሄደ ይገኛል።
ኢትዮጵያ የልማት ትልሞቿን እንዲሁም ስኬቶቿን በመረጃ እና በአሃዛዊ ማስረጃ መሰነድ ከጀመረች መሰነባበቷን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
ይህ እርምጃ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በሌሎች በሚደገፉና በተበታተኑ የመረጃ ቋቶች ላይ የነበራትን ሙሉ ጥገኝነት ለመቅረፍ ያሳየችውን ከፍተኛ ቁርጠኝነት ማረጋገጫ መሆኑን አመልክቷል።
ይህ አዲስ ምዕራፍ የሀገሪቱን የመረጃ ሉዓላዊነት በተግባር በማረጋገጥ፣ ኢትዮጵያ በራሷ መረጃ ላይ ተመስርታ እንድትወስንና የራሷን የልማት መስመር እንድትተልም አስችሏታል።
በዚህም መሠረት፤ በዛሬው ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ ልማትና የመረጃ ሉዓላዊነት ጉዞ ያመጣቸው ስኬቶችና የወደፊት አቅጣጫዎች በጥልቀት እንደሚዳሰሱ ጽህፈት ቤቱ ገልጿል።