በጉራጌ ዞን የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች ልማት የአርሶ አደሩን ምርታማነት አሳድጓል - ኢዜአ አማርኛ
በጉራጌ ዞን የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች ልማት የአርሶ አደሩን ምርታማነት አሳድጓል
ወልቂጤ፣ ግንቦት 10/2018 (ኢዜአ):-በጉራጌ ዞን የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን በማልማት ምርታማነታቸውን ማሳደግ እንደቻሉ አርሶ አደሮች ገለጹ።
በዞኑ እኖር ወረዳ የከረቤድ ቀበሌ አርሶ አደር ሞሳ በሽር የተሻሻለ የቡና ተክል በማልማት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡ ናቸው።
በመጪው ክረምት የሚተከል ከ1 ሺህ በላይ የተሻሻሉ የቡና ችግኞችን ለመትከል የጉድጓድና የተፈጥሮ ማዳበሪያ እያዘጋጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የቡና ልማትን ለማስፋፋትም በመንግስት በኩል ምርታማ የሆኑና በሽታን መቋቋም የሚችሉ የቡና ችግኞች ከማግኘታቸው ባለፈ የባለሞያ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በአበሽጌ ወረዳ ጣጤሳ ቀበሌ አርሶ አደር ሙርሺዳ አብዶ በበኩላቸው ከመንግስት በድጋፍ የተረከቧቸውን የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ምርት በመስጠት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የተሻሻሉት የቡና ዝርያዎች በምርትና በሽታን በመከላከል ረገድ ውጤታማ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ሥራውን ይበልጥ ለማሳካትም በጥላ ዛፍ ሥር በመከለልና የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጠቀም እንክብካቤ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የቡና ልማቱን አጠናክሮ ለማስቀጠልም ዘንድሮም 250 የተሻሻሉ የቡና ችግኞችን ለመትከል ጉድጓዶችን በመቆፈር የተከላ ጊዜውን እየጠበቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ በበኩላቸው፣ በዞኑ በምርታማነታቸው የተረጋገጡ የቡና ዝርያዎች ለአርሶ አደሩ መቅረባቸው ከዘርፉ የሚገኘውን ውጤት እያሳደገው ነው።
ለዚህም የዞኑን የቡና ማሳ ሽፋን 55 ሺህ 400 ሄክታር መድረሱን የገለጹት አቶ አበራ፣ ምርታማነትም በአማካይ በሄክታር ከስምንት ኩንታል በላይ መድረሱን ጠቅሰዋል።
የቡና ልማቱን በማጠናከር የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማስፋት በዘንድሮ ዓመትም የተሻሻለ የቡና ችግኝ ተከላ ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።