ቀጥታ፡

በገላን ጉራ ያረፈው አሻራችን የኢንዱስትሪ ፓርክ ብቻ ሳይሆን፣ የአካባቢውን ገጽታ እና የነዋሪዎቹን ሕይወት ሙሉ በሙሉ ከስር መሠረቱ የለወጠ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2018(ኢዜአ)፦ በገላን ጉራ ያረፈው አሻራችን የኢንዱስትሪ ፓርክ ብቻ ሳይሆን፣ የአካባቢውን ገጽታ እና የነዋሪዎቹን ሕይወት ሙሉ በሙሉ ከስር መሠረቱ የለወጠ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ያስተላለፉት ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል

ገላን ጉራ የብልጽግና አሻራ!

የመዲናችን የብልጽግና ጉዞ ስፋትና ጥልቀት የሚለካው፣ የከተማዋን እምብርት በማስዋብ ብቻ ሳይሆን፣ ትናንት በአግባቡ ያልተጠቀምንባቸውን ሀብትና አካባቢዎችን ዓይናችንን ገለጥ በማድረግ ተመልክተን የልማትና የዕድገት ማዕከል በማድረግም ጭምር ነው።


 

ከ5 ዓመት በፊት፣ ምንም የሚታይ መሠረተ ልማት ያልነበረው የገላን ጉራ አካባቢ፣ ዛሬ ላይ የታሪክ ምዕራፉ ተቀይሮ የከተማችንን ሁለንተናዊ የልማት ከፍታና መዋቅራዊ ሽግግር የሚያሳይ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ መስተጋብር ማዕከል ሆኗል። ዛሬ በዚህ ስፍራ ያረፈው አሻራችን የኢንዱስትሪ ፓርክ ብቻ ሳይሆን፣ የአካባቢውን ገጽታ እና የነዋሪዎቹን ሕይወት ሙሉ በሙሉ ከስር መሠረቱ የለወጠ ነው።


 

ለአብነትም:-

1. በአዲስ አበባ የመጀመሪያው እና ትልቁ ባለ 325 ሜትር ርዝመትና 60 ሜትር ስፉት ዘመናዊ ድልድይ፣

2. 21 ነጥብ 73 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው (ቃሊቲ ቀለበት -ቱሉዲምቱ

እና ቃሊቲ ቀለበት - ቂሊንጦ አደባባይ) የኢትዮጵያ የንግድ ኮሪደርን ያሳለጠ እና ቀጥታ ከአየር መንገድ ካርጎ የሚያገናኝ ዘመናዊ የመንገድ መሠረተ ልማት፣

3. የከተማችንን የመኖርያ ቤት አቅርቦት ችግር ለማቃለል አዲስ ከተማን የመገንባት ያህል የሆነ 60 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣

4. ከካዛንቺስ አካባቢ ለልማት ለተነሱ ነዋሪዎቻችን የገነባነው ምቹና የተቀናጀ ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር የሚገኝበት፣

5. የኅብረተሰባችንን ጤና በላቀ ደረጃ ለመጠበቅ በከተማችን በትልቅነቱ ቀዳሚ የሆነው የገላን ትሯማ ሆስፒታል ግንባታ፣

6. በአካባቢው ለዚሁ ልማት ለእርሻ ሲጠቀሙበት የነበረውን መሬት ለለቀቁልን አርሶ አደሮች የተቀናጀ ዘመናዊ የግብርና ልቀት ማዕከል ግንባታ፣

7. መንፈስን የሚያድሱ ሰፋፊ አረንጓዴ ስፍራዎችና ፓርኮች፣

8. የስፖርት ማዘውተሪያዎችና የልጆች መጫወቻዎች፣ ለእናቶች ሰፊ የስራ ዕድል የሚፈጥር የእንጀራ ፉብሪካ ግንባታና የመሳሰሉት የብልፅግና አሻራዎች ደምቀው አካባቢውን ከመሐል ከተማ የበለጠ ተመራጭ አድርገውታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም